
ጎንደር፡ ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ማኅበረሰቡን በቅንነት እና በታማኝነት ላገለገሉ ተቋማት እና ባለሙያዎች ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።
“ማገልገል ክብር ነው፤ በቅንነት ማገልገል ደግሞ ድርብ ክብር ነው” በሚል መሪ መልዕክት የመንግሥት ሠራተኞች ቀን በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተከብሯል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በትጋት ሕዝባቸውን ላገለገሉ መሪዎች እና ባለሙያዎች ዛሬ ዕውቅና መሰጠቱ ለነገ ስንቅ መቋጠር ነው ብለዋል።
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ጀግኖች የልማት አርበኞች የሚዘከሩበት ቀን እንደሚኖርም ተናግረዋል።
መሪነት መመሪያን ተከትሎ የማኅበረሰብን ችግር መፍታት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በተቋማት ውስጥ ያሉ አቅሞችን በመለየት ለተቋም አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል በግብዓትነት መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ነጻነት መንግሥቴ ዛሬ ዕውቅና እና ሽልማት ያገኙ ተቋማት እና ግለሰቦች ለሌሎች አርዓያ የሚኾኑ ናቸው ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በየዘርፉ ጠንክረው ለሠሩ እና በታማኝነት ላገለገሉ ባለሙያዎች ገንዘብ እና ሜዳሊያ ተበርክቶላቸዋል።
ማኅበረሰብ እና ሀገርን አገልግለው በዕድሜ ምክንያት በጡረታ ለተገለሉ 32 የመንግሥት ሠራተኞች ተቋሙ የሜዳሊያ፣ የምሥክር ወረቀት እና የገንዘብ ሽልማት ማበርከቱንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ- ማርታ አዱኛ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!