የነዳጅ ውጤቶችን ግብይት

30
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ነዳጅ በአብዛኛው ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለ ምርት ነው። በሀገራችን በኹሉም ዘርፍ የነዳጅ ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እያደገ መጥቷል።
አኹን ላይ ነዳጅ ሕጋዊ ባልኾነ ቦታ ወይም አዋጁ እንዲሸጥ ባልፈቀደበት ቦታ እና ከዋጋው በላይ ሲሸጥ ይስተዋላል።
የነዳጅ ግብይትን እንዲፈጽሙ ኀላፊነት የተሰጣቸው አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች ሳይቀር ነዳጅ እያለ የለም የሚሉበት አጋጣሚም እንዳለ በተጠቃሚዎች ይነሳል።እንደዚህ አይነት አካሄድ ከሚፈጥረው የግብይት ሚዛን መዛባት በተጨማሪ ከጋዝ ተፈጥሯዊ ባህሪ የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። እነዚህን እና መሰል ተግባሮችን ለመቆጣጠር አዋጁ በ2017 ዓ.ም ተሻሽሎ ወጥቷል።
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የሕግ ባለሙያ ፍቅር በለጠ በአዲሱ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት አዋጅ ቁጥር 1363/2017 የነዳጅ ውጤቶችን ግብይት እና ስርጭት ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ እንደኾነ ገልጸዋል። በዚህ አዋጅ አንቀጽ 2(1) ላይ የነዳጅ ውጤቶችን ምንነት በትርጉም ደረጃ ማስቀመጡን ይገልጻሉ። በዚሁ አንቀጽ እንደተቀመጠው “የነዳጅ ውጤቶች” ማለት የተፈጥሮ ድፍድፍ ነዳጅን፣ ፔትሮሊየም ጋዝን፣ ባዮ ፊውልን ወይም ሲንተቲክ ነዳጅን ከማጣራት ወይም ከማቀናበር የተገኘ ንፁህ ወይም አግባብ ባለው መንገድ የተደባለቀ የነዳጅ ውጤት ኾኖ ቤንዚንን፣ ኬሮሲንን፣ ናፍጣን፣ ቀላል እና ከባድ ጥቁር ናፍጣን፣ የአውሮፕላን ነዳጅን እና የመሳሰሉትን የሚያካትት ትርጉም እንደተሰጠው ያብራራሉ።
በአዋጁ አንቀፅ 2 (12) መሠረት ነዳጅ ማደያ ማለት “የነዳጅ ውጤቶችን ከአከፋፋይ ገዝቶ ለመጨረሻ ተጠቃሚዎች በችርቻሮ የሚሸጥ ሰው ነው” የሚል ትርጉም እንደተሰጠው አብራርተዋል።በዚህ ምክንያት ማንኛውም የነዳጅ ማደያ ሊያከብራቸው የሚገቡ ግዴታዎች በአዋጁ ላይ እንደተቀመጠ ይገልጻሉ።ከግዴታዎች መካከልም ማንኛውም ለሚያቋቁመው ለእያንዳንዱ የነዳጅ ማደያ በባለሥልጣኑ የሚጠየቁ መሥፈርቶችን አሟልቶ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ማግኘትን እንደሚያስገድድ አብራርተዋል።የነዳጅ ውጤቶችን ውል ከገባው አከፋፋይ ብቻ በመግዛት እና በመረከብ ነዳጅ ማደያው ውስጥ እንዲራገፍ የማድረግ ግዴታም አለበት ነው ያሉት።
የነዳጅ ውጤቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር ያለመቀላቀል፣ ጥራቱን ሊያጓድል ከሚችል ማናቸውም ድርጊት የመቆጠብ እና ለመጨረሻ ተጠቃሚዎች በችርቻሮ የመሸጥ ኀላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።የዋጋ ቁጥጥር የሚደረግባቸውን የነዳጅ ውጤቶች አግባብነት ያለው የመንግሥት አካል በወሰነው ዋጋ ብቻ የመሸጥ ግዴታ አለበት ብለዋል ባለሙያዋ።ማንኛውም ማደያ ለመጨረሻ ተጠቃሚዎች ያልተቆራረጠ የ24 ሰዓት የሽያጭ አገልግሎት የመስጠት፤ ነዳጅ በማደያ ውስጥ እያለ የሽያጭ አገልግሎት ማቋረጥ እንደማይችሉም ሕጉ ያዝዛል ብለዋል።በአዋጁ የተቀመጡትን ግዴታዎች አለማክበር አሥተዳደራዊ እርምጃዎች እንደሚያስወስድ በዚኹ አዋጅ የተቀመጠ መኾኑንም ነው የሕግ ባለሙያዋ ያብራሩት።
በአዋጁ የተቀመጡትን ክልከላዎች መተላለፍ የወንጀል ተጠያቂነትንም ያስከትላል ነው ያሉት። በአዋጁ ከተቀመጡት አሥተዳደራዊ ቅጣቶች መካከል የተወሰኑትን ለማንሳት ያክል፦
👉የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጭ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ ቦታ እና የግብይት ሥርዓት ውጭ ሲሸጥ የተገኘ ወይም በመመሪያ በተወሰነው መሠረት አደጋ ያስከትላሉ በተባሉ መያዣዎች ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ሰው የተያዘው የነዳጅ ውጤት ተወርሶ ከሦሥት ዓመት እስከ አምሥት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከብር 350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ እንደሚያስቀጣ አስገንዝበዋል፡፡
👉የነዳጅ ውጤቶችን ኾን ብሎ ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ያቀረበ ማንኛውም ሰው ነዳጁ እንዲወገድ ተደርጎ ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከብር 350 ሺህ እስከ 500 ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ አመላክተዋል፡፡
👉የዋጋ ቁጥጥር የሚደረግባቸውን የነዳጅ ውጤቶች መንግሥት ከተመነው የመሸጫ ዋጋ በላይ ሲሸጥ የተገኘ የግብይት ተዋናይ በመጀመሪያ ጥፋት ከብር 350 ሺህ እስከ 500ሺህ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፤ ድርጊቱን በተደጋጋሚ ከፈጸመ ከሦሥት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከብር 300 ሺህ እስከ 500ሺህ በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጣ መደንገጉን ገልጸዋል፡፡
👉የተረከባቸውን የነዳጅ ውጤቶች ከተፈቀደለት የማጓጓዣ መስመር ውጭ ሲያጓጉዝ፣ ከተፈቀደለት ማራገፊያ ውጭ ሲያራግፍ ወይም ወደ ጎረቤት ሀገር በኮንትሮባንድ ሲያጓጉዝ የተገኘ ማንኛውም ሰው የተያዙት የነዳጅ ውጤቶች ተወርሰው ከአምስት ዓመት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከብር 400ሺህ እስከ 7ዐዐ ሺህ በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ነው የገለጹት፡፡
👉አግባብ ካለው አካል የጽሑፍ ፈቃድ ሳያገኝ የነዳጅ ውጤቶችን የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ሰው የተያዘው ነዳጅ ተወርሶ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከብር 300ሺህ እስከ 500ሺህ በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጣ አመላክተዋል።
👉የባለሥልጣኑን ወይም አግባብ ያለውን አካል የቁጥጥር ሂደት የተቃወመ፣ ያሰናከለ ወይም በማንኛውም መንገድ ተፅዕኖ ያደረሰ ማንኛውም ሰው ከሦሥት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት እና ከብር 200ሺህ እስከ 500ሺህ ብር መቀጮ ይቀጣል ነው ያሉት።
👉በዚህ አንቀጽ የተመለከቱት ድርጊቶች የሕግ ሰውነት ባለው አካል የተፈፀሙ በኾነ ጊዜ ከብር 600ሺህ እስከ 1ሚሊዮን ብር መቀጮ እንደሚያስቀጣ ገልጸዋል።
👉የነዳጅ ግብይት የዲጂታል ሥርዓት ግዴታን የጣሰ፣ ያጭበረበረ፣ ተግባራዊ ያላደረገ የግብይት ተዋናይ ከ2 ዓመት በማይበልጥ እስራት እና እስከ 300ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ የሕግ ባለሙያዋ አብራርተዋል።
በአዋጁ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ተላልፎ ለሁለተኛ ጊዜ በመፈጸም ጥፋተኛ ኾኖ የተገኘ የግብይት ተዋናይ በዚህ አንቀጽ ከሚጣልበት ቅጣት በተጨማሪ ድርጅቱን ለአምሥት ዓመታት እንዲዘጋ የሚያስገድድ ቅጣት እንደሚጣልበት አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“ለዜጎች የጋራ ተጠቃሚነት በቅንጅት መሥራት ይገባል” ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)
Next articleሥንቶቻችን ሥራችንን በዕቅድ እንመራ ይኾን?