የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዘርፍን ለማዘመን የ25 ዓመታት የትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ይፋ ተደረገ።

32
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ከ2025 እስከ 2050 ድረስ ለማዘመን ያለመ የ25 ዓመታት የትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ በይፋ መጀመሩ ተገልጿል።
ይህ ሰፊ ዕቅድ በዘርፉ ለረጅም ጊዜ የታዩትን ውስብስብ ችግሮች ለመቅረፍ እና ኢንዱስትሪውን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።የኮንስትራክሽን ዘርፉ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ቢመጣም የፕሮጀክቶች አፈጻጸም በጊዜ አለመጠናቀቅ፣ የተወዳዳሪነት እና የብቃት ማነስ እንዲሁም የፋይናንስ እጥረት የመሳሰሉ ፈተናዎች በስፋት ይስተዋላሉ።
ይህንን ችግር ለመፍታት የተቋቋመው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ በዘርፉ የሚታዩትን ክፍተቶች ሙሉ ለሙሉ ለመሙላት ጥረት እያደረገም ይገኛል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢኒሼቲቩ በዘርፉ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት እና ጠንካራ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎችን በማቋቋም የግንባታ ሥራዎችን በጊዜ እና በጥራት ለማጠናቀቅ ያለመ መኾኑን ተናግረዋል።
ይህ ርምጃ ሀገሪቱ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የምትፈልገውን ዕድገት እና ልማት ለማምጣት ወሳኝ እንደኾነም ገልጸዋል። የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ይፋ የተደረገው ኢኒሼቲቭ በሚቀጥሉት ዓመታት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን በስፋት እንዲጠቀም፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ የተሻለ እንዲኾን እና ብቃት ያለው የሰው ኃይል እና የሥራ ተቋራጭ እንዲፈጠር ያግዛል ብለዋል።
በተጨማሪም የግንባታ ባለሙያዎች እና ድርጅቶች በብቃት ምዘና እንዲያልፉ በማድረግ፣ ተወዳዳሪ እና ጠንካራ ተቋራጮች ለመገንባት ኢኒሼቲቩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል። ይህ የ25 ዓመታት የለውጥ ዕቅድ በሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ሥር የሰደዱ ችግሮችን በመፍታት በዘርፉ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ተመሥገን ዳረጎት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየምሥራቅ ጎጃም ዞን የእንስሳት ተዋፅዖ አቅርቦትን ለማሳደግ እየሠራ ነው።
Next articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክት፦