
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ነፈሰ ጡር እናቶች ለወባ የመያዝ ዕድላቸው ሰፊ እንደኾነ ይነገራል።
ወይዘሮ እናት ከበደ በእርግዝና ወቅት የወባ በሽታ ይዟቸው ነበር። ወይዘሮ እናት የሚኖሩበት አካባቢ ረግረጋማ በመኾኑ በተደጋጋሚ በወባ በሽታ እንደሚጠቁ ይናገራሉ፡፡በአንድ ወቅት የስምንት ወር ነፍሰጡር እያሉ በወባ በሽታ ተይዘው ነበር።ወደ ሕክምና ተቋም ሄደው ለመመርመር እና መድኃኒት ለመውሰድ ግን አልደፈሩም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ መድኃኒቱ ጽንሱን ያስወርደዋል በሚል የልጅ ጉጉት እንደኾነ ይናገራሉ፡፡
እየዋለ ሲያድር በሽታው ተባብሶ ወደ ሕክምና ተቋም ለመሔድ ተገደዱ። ነገር ግን የጓጉለትን ጽንስ ማትረፍ አለመቻላቸውን አስታውሰውናል፡፡ወይዘሮ እናት ለሁለተኛ ጊዜ ባረገዙበት ወቅት የወባ በሽታ ስሜት እንደተሰማቸው ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ መመርመራቸውን ጠቁመዋል፡ሐኪሞች በሰጧቸው ምክረ ሃሳብም መድኃኒት በአግባቡ በመውሰድ ልጃቸውን በሰላም መገላገላቸውን ነው የተናገሩት።በአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ዳምጤ ላንከር ነፍሰ ጡር እናቶች ከሌሎች ሰዎች በበለጠ ለወባ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ይላሉ።
ለመኾኑ በእርግዝና ወቅት ወባ ቢከሰት ምን ጉዳቶችን ያስከትል ይኾን?




እነዚህን ከባድ ችግሮች ለመከላከል ነፍሰ ጡር እናቶች ወባን አስቀድመው መከላከል እና በሕመም ሲጠቁ በፍጥነት ሕክምና ማግኘት ወሳኝ ነው ይላሉ አስተባባሪው።

ወባን ለመከላከል ቀላል ነው የሚሉት አስተባባሪው ውኃ የሚያቁሩ ቦታዎችን ማፋሰስ እና ማዳፈን፣ የወባ ትንኝ እንዳይራባ መከላከል ሁነኛ መፍትሔ ነው ይላሉ።በኬሚካል የተነከረ አጎበር ሁልጊዜ መጠቀም ከወባ ትንኝ ንክሻ ለመዳን እንደሚጠቅምም ጠቁመዋል።የፀረ ትንኝ ወይም ፀረ እጭ ኬሚካሎችን መጠቀም ሌላው መፍትሔ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ከመከላከያ መንገዶች በተጨማሪ፣ ማንኛውም የወባ በሽታ ምልክት ሲሰማ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ እና የታዘዙ መድኃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ አስፈላጊ መኾኑንም ጠቁመዋል።መድኃኒቱ ፅንሱን ይጎዳል የሚል አስተሳሰብ ትክክል አለመኾኑን የተናገሩት አስተባባሪው የታዘዙትን መድኃኒቶች በአግባቡ በመውሰድ ከሚከሰተው ጉዳት መጠበቅ እንደሚገባም አብራርተዋል።
ዘጋቢ: ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን