የሀገር በቀል ችግኞች ለባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ ትርጉማቸው የተለየ ነው።

13
ባሕር ዳር: ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና ተጠሪ ተቋማት መሪዎች እና ሠራተኞች በአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሄደዋል፡፡
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ የችግኝ ተከላው እንደ ሀገር ‘’በመትከል ማንሰራራት’’ በሚል መሪ መልዕክት እየተሠራ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አካል መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የተተከሉት ችግኞች አብዛኞቹ ሀገር በቀል መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሀገር በቀል ችግኞች እንደ ባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ የተለየ ትርጉም አላቸው፤ ለዚህ ምክንያቱ ለመድኃኒትነት፣ ለእደ ጥበብ ምርቶች የሚያገለግሉ እና የአየር ንብረትን ለመጠበቅ ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር በርሃማነትን፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ችግኞችን በመትከል፣ አካባቢን መንከባከብ ይገባል ብለዋል፡፡ ችግኝ መትከል የአየር ንብረት ለውጡን ለመከላከል የሚያግዝ በመኾኑ በትኩረት የሚሠራ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ የሥራቸው አንድ አካል በማድረግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
በባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጋሻየ መለሰ ሀገር በቀል ችግኞች ሥነ ምኅዳርን ከመንከባከብ ባለፈ ለቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ይህም ራሳቸው ሀገር በቀል ዛፎች ቅርስ ናቸው፤ ሌላው ጥንታዊ ቅርሶች የተሠሩት በሀገር በቀል እጽዋት በመኾኑ ቅርሶችን ለመጠገን እና ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ የተሠሩበት ዛፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ችግኞችን ከመትከል ባለፈም በየጊዜው እንክብካቤ እና ክትትል አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ የተተከለበት ቦታም ለእንክብካቤ ምቹ በመኾኑ በየጊዜው በዕቅድ በመመራት እንደሚንከባከቡ ተናግረዋል፡፡ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የተሳተፉት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሠራተኛ አስካል አምባቸው ችግኝ ተከላ ለአካባቢ ጥበቃ ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ልጆቻችን እንደምንከባከበው ሁሉ ችግኞችን በየጊዜው ተንከባክቦ ማሳደግ ይገባናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየሩዝ ምርትን ለማሳደግ ምን እየተሠራ ነው ?
Next articleአስበው የሠሩት ብርቱው ሰው