
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች፣ ከፖሊስ፣ ከአድማ መከላከል እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
እየተሠራው ባለው ሥራ መልካም ውጤት እየተገኘ መኾኑን ነው የገለጹት። በርካታ የታጠቁ ኃይሎች የያዙት አቋም ትክክል አለመኾኑን በመገንዘብ ሰላማዊ መንገድን እየመረጡ መኾናቸውን አስታውቀዋል። የታጠቁ ኃይሎች ሰላማዊ አማራጭን ተቀብለው የሚገቡበትን አካሄድ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባልም ነው ያሉት።
መገዳደል ለማንኛውም ዜጋ አዋጭ እና ጠቃሚ አይደለም ያሉት ኀላፊው የክልሉ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ የክልሉ ሕዝብ በሰላም ሠርቶ እንዲኖር ለማድረግ የታጠቁ ኃይሎች ሰላማዊ አማራጭን መቀበል እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት። ውጤት የሚመጣው በግጭት ሳይኾን በሰላማዊ አማራጭ ነውም ብለዋል።
የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ የሚገቡ በርካታ
ኃይሎች እንዳሉ ሁሉ አላስፈላጊ ድርጊት የሚፈጽሙ እንዳሉም አንስተዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች መንገድ እንዘጋለን የሚሉ ኃይሎች እንዳሉ ያነሱት ኀላፊው ይህን ተግባር የጸጥታ ኃይሉ እየመከተው እና እያከሸፈው መኾኑን ተናግረዋል።
እንዲህ ዓይነት መንገድ ለሕዝብ የማይጠቅም የጥፋት መንገድ መኾኑን ነው የገለጹት። የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ የጸጥታ ኃይሉ ዋጋ እየከፈለ መኾኑን ነው የተናገሩት። ሕዝቡም ለጸጥታ ኃይሉ እየሰጠው ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
ሰላም የሚረጋገጠው በጸጥታ ኀይሉ ብቻ አይደለም ያሉት ኀላፊው ሰላም የሚረጋገጠው የሕዝቡ ተሳትፎ ሲኖር ነው ብለዋል። ሕዝቡ ለሰላም ያለውን ቀናኢነት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አስገንዝበዋል። የክልሉ ሕዝብ በግጭቱ ተጎጂው ራሱ ስለኾነ ሰላም እንዲመጣ ዋጋ እየከፈለ ነው ብለዋል። የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ሕዝቡ ከጸጥታ ኀይሎች ጋር ተባብሮ እንዲሠራም አሳስበዋል።
የአማራ ክልልን ሰላም ማረጋገጥ ለመላው ኢትዮጵያ ሰላም መረጋገጥ ወሳኝ እንደኾነም አንስተዋል። የተጀመረውን ሰላም ለማስቀጠል የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኀይሉ ዋጋ እየከፈለ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የሕግ ማስከበር ሥራው በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ኀላፊው ሕግ እና ሥርዓት ካልተከበረ ሰላም አይኖርም ነው ያሉት። ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር በሚደረገው ሂደት ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የታጠቁ ኀይሎች ሰላማዊ አማራጭን እንዲቀበሉ ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ከሰላም አማራጭ ጎን ለጎን በዘረፋ ሥራ ላይ በተሰማራው ኀይል ላይ የሚደረገው የሕግ ማስከበር ሥራ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። በክልሉ እየተደረገ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ ውጤት እያስመዘገበ መኾኑንም አስታውቀዋል። የታጠቁ ኀይሎችን በሰላም መንገድ ለማስገባት እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች ነው ያሉት ኀላፊው በአንዳንድ ቦታዎች በተበተነ ሁኔታ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በቡድን እየኾኑ የሚገቡት ታጣቂዎች ቁጥር ብዙ ነው ብለዋል።
ታጣቂዎች እስከመሪዎቻቸው ድረስ እየገቡ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። በሰላም እንዲገቡ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል። የሰላም አማራጭን በማይቀበሉ ኀይሎች ላይ ግን አሁንም ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ሕግ እና ሥርዓት ካልተከበረ የተጀመረው ሰላም ዘላቂ እንደማይኾንም ገልጸዋል። በሰላም እንዲገቡ የማድረግ እና ሕግ የማስከበር ሥራዎች ተጣጥመው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት።
በየአካባቢው ከሕዝብ ጋር በመወያየት ጫና እንዲፈጠር የተሠራው ሥራ ውጤት ማስመዝገቡንም ገልጸዋል። የሕዝብ ግንኙነት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል። ዘራፊ ኀይሉ አሁንም በሕዝብ ላይ በደል እየፈጸመ ነው ያሉት ኀላፊው በዘራፊው ቡድን ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት። ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት መኾኑንም ተናግረዋል። ሁሉም ለሰላም መከበር አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!