የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ የተሰማሩ የጸጥታ አካላትን ቤተሰቦች መደገፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።

30

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ ዋጋ እየከፈሉ መኾናቸውን ገልጸዋል። በሕግ ማስከበር ሥራው አስተዋጽኦ እያደረጉ ላሉት የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ሕዝቡ እያደረገው ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መኾነው ነው የተናገሩት።
የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ሃብት እና ንብረት እንዲጠበቅ፣ መሬታቸው በዘር እንዲሸፈን በማድረግ፣ ሰብላቸውን በማረም፣ ቤተሰቦቻቸውን በመንከባከብ እያደረገው ያለው አስተዋጽኦ ጥሩ ነው ብለዋል።
ሕግ በማስከበር ሥራ የተሠማሩትን የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ዋጋ እየከፈሉ ያሉት ለሕዝብ ነው ያሉት ኀላፊው ቤት እና ንብረታቸውን፣ ልጆቻቸውን ትተው ዋጋ እየከፈሉ ያሉት ለሕዝብ ሰላም ነው ብለዋል። ለሕዝብ ሰላም ሲል ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ኃይሎችን መደገፍ ለሰላም መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ መኾኑን ነው የተናገሩት። እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በግንባር ኾኖ ሕግ እና ሥርዓት እያስከበሩ ላሉ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በዘር ያልተሸፈነው ማሳቸው በዘር እንዲሸፈን፣ በዘር የተሸፈነው ማሳቸው አረም እንዲታረም፣ እንዲኮተኮት፣ ማዳበሪያ እንዲጨመር ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት። ለሕዝብ ሲሉ የወጡ ኃይሎች ማሳ ጦም ማዳር እንደማይገባው ተናግረዋል።
የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ልጆች በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ የትምህርት ቁሳቁስ እንዲሟላላቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል። ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል በግዳጅ ላይ ያሉ ኃይሎችን ቤተሰቦች ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በግዳጅ ላይ ያሉ ኃይሎችን ቤት የመሥራት፣ ቤተሰቦቻቸውን የመንከባከብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተናግረዋል። በግዳጅ ያሉ ኃይሎች አለኝታ ሕዝቡ ነው ያሉት ኀላፊው ከሕዝብ ነው የወጡት፣ ለሕዝብ ነው የሚያገለግሉት ብለዋል። መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ቤተሰቦችን የሁሉም መኾኑንም ገልጸዋል።
ሰላም እና ልማት እንዲመጣ ከሁሉም በላይ ሕግ ማስከበር አለበት፣ ሁሉም ለሕግ ማስከበር ሥራው አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ነው ያሉት። የክልሉ መንግሥት ለሚሊሻ እና ለሰላም አስከባሪ ኃይሎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
ለሕዝብ ሰላም እናስከብር ብለው የወጡ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ዘራፊ ኃይሉ ጉዳት አድርሶባቸዋል ያሉት ኀላፊው ንብረታቸው መዘረፉን፣ ቤታቸው መቃጠሉን፣ የሕይዎት መስዋዕትነት መክፈላቸውን፣ ቤተሰቦቻቸው መንገላታታቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ሃብት እና ንብረት ለወደመባቸው የካሳ እና የድጎማ ተግባር እየፈጸመ መኾኑን ተናግረዋል። ለሕዝብ ሰላም ሲሉ መስዋዕትነት ለሚከፍሉ ኃይሎች በሕግ እና በደንብ መሠረት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ከመንግሥት ባሻገር ሕዝቡን ሰላም እና ደህንነቱን ለመጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚገኙ ኃይሎችን መደገፍ አለበት ብለዋል። ሰላም በኾነ ጊዜ ሠርተው የሚበሉ፣ ችግር ሲፈጠር በራሳቸው ተነሳሽነት ወጥተው ሰላም የሚያስከብሩ አለኝታዎች ናቸው ብለዋል።
ከሕዝብ የወጣው፣ ለሕዝብ የወጣው እና ለሕዝብ የቆመው የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኃይል ድጋፍ ከተደረገለት የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠል ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል ነው ያሉት። ሕግ የሚያስከብረው አካል በተደራጀ መልኩ ግዳጁን እንዲፈጽም ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበጀት ዓመቱ 75 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን አስታወቀ።
Next articleውጤት የሚመጣው በግጭት ሳይኾን በሰላማዊ አማራጭ ነው።