
አዲስ አበባ: ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ ንፁህ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ የመኾን ራዕይን ይዞ እየሠራ ያለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫዎችን፣ ማስተላለፊያዎችን እና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን በመገንባት እና በማሥተዳደር የኤሌክትሪክ ኃይል የጅምላ ሽያጭን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገራት በማቅረብ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንዳሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ 20 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች አሉት። ባለፉት ስድስት ዓመታት ከነበረው 7 ሺህ 910 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አሁን ላይ 3 ሺህ 784 ሜጋ ዋት እድገት አሳይቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 308 የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ከ20 ሺህ 700 በላይ ሰርኪዩት መስመር 145 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከ31 ሺህ 400 በላይ ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው 361 ትራንስፈርመሮች ያሉት መኾኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።
በዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል በተከፈለ ካፒታል 585 ቢሊዮን ብር እና በተፈቀደ ካፒታል 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር የመጀመሪያ ደረጃ ላይ መገኘቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2017 በጀት ዓመት 25 ሺህ 423 ጊጋ ዋት በሰዓት ለማምረት አቅዶ 29 ሺህ 480 ጊጋ ዋት በሰዓት ለማመንጨትም መቻሉን አመላክተዋል።
በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ የኃይል ጭነት 4 ነጥብ 916 ሜጋ ዋት ኾኖ መመዝገቡን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል። በዚህም በበጀት ዓመቱ 25 ነጥብ 1 ቴራ ዋት በሰዓት ኢነርጂ የተሸጠ ሲኾን ከዚህ ውስጥም 93 በመቶ ለሀገር ውስጥ እና 7 በመቶ ለውጭ ተሽጦ በድምሩ 75 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ገልጸዋል። ለዚህ ውጤት መገኘት የሕዳሴ ግድብ የጎላ ሚና እንደነበረው ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመሠረተ ልማት ላይ የሚታዩ የንብረት ስርቆቶች ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በእቅዱ መሠረት ተንቀሳቅሶ ሥራዎችን መሥራት ፈተና መኾናቸውን ተናግረዋል።
ጥራት ያለው የኃይል አቅርቦትን ለማጠናከር የሚሠሩ ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መኾኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ የራሱ የኾኑትን የኤሌክትሪክ ሀብቶችን በመጠበቅ ሀገራዊ ኀላፊነት እና አደራውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት እንደ ሀገር የተሻለ የኃይል አቅርቦትን ለኅብረተሰቡ ለማድረስ በትኩረት እየሠራ እንዳለም ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን