
ባሕር ዳር: ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበራዊ ሚዲያ አዳዲስ ዝማኔዎችን እየጨመረ፣ የተጠቃሚውን ቁጥር አያሳደገ እና ተጽዕኖ እየፈጠረ የቀጠለ የዘመኑ ውጤት ነው ።
ሰዎች ርቀት አልባ እንዲኾኑ፣ በየትኛውም ቦታ እና ኹኔታ መገናኘት እንዲችሉ ትልቅ አገዛን እያደረገ ነው። የጠፉትን ወዳጆች በማገናኘት፣ ደጋፍ የሚሹትን እንዲረዱ በማድረግ፣ ድንበር አልባ ወዳጅነት እና ትብብር እንዲፈጠር በማድረግም በጎ አበርክቶ አለው።
ሌሎች በጎ ጎኖቹንም መዘርዘር ይቻላል። በአንጻሩ ግን አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚያደርሳቸው የጤና እክሎች ትኩረት የሚሹ ናቸው።
የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ድረ ገጽ ላይ በወጣ ጽሑፍ የፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ፣ የቴክኖሎጂ እና ጤና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ብሪያን ፕሪማክ ማኅበራዊ ሚዲያ የሰዉ ልጅ ሕይወት ውስጥ ዘልቆ የገባ በመኾኑ የሚያደርሰውን የጤና ችግር ለመከላከል የሕክምና ባለሙያዎች እገዛ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል::
በገጹ እስከ 2030 ባለው የአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ላይ ካልተመጠነ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚያደርሰው የጤና እክል ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቅሷል።
ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ መልካም ያልኾነው ልምድ ልቅ ወይም ያልተገደበ ተጠቃሚነት ነው። ይህም ሰዎች መቆጣጠር በማይችሉት ኹኔታ ብዙ ጊዜን በማኅበራዊ ሚዲያ እንዲያሳልፉ ያደርጋል። በሕይወት ጠቃሚ ከምንላቸው የቤተሰብ፣ የሥራ እና መሰል ግንኙነቶች በላይ ትኩረት ሰጥቶ በመጠቀም ሱሰኛ ያደርጋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ባልቻልንባቸው ጊዜያት ጤናችንን የሚያውክ የሥነ ልቦና ጉዳትን ያደርሳል። ግላዊ ብቻ የኾነ ማንነት አንዲኖረን ያደርጋል፤ የእንቅልፍ መዛባት ይፈጥራል፤ የአይን ጤናን ያቃውሳል፤ ጭንቀትን እና ፍርሀትን ይፈጥራል፣ ለራስ የሚሰጥ ግምት ደካማ እንዲኾን ያደርጋል።
ከአጠቃቀም ችግር ጋር ተያይዞ ለሚከሰት የሥነ ልቦና እና የሥነ አዕምሮ ጤና ችግር የሕክምና ባለሙያዎች በሚሰጡት ድጋፍ ሊሻሻል ቢችልም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የምናጠፋውን ጊዜ ግን ልንቆጣጠረው የምንችለው እና የተመጠነ የጊዜ ቆይታ ያለው ሊኾን ይገባዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን