ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማር ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ የቀድሞ የትምህርት ሚኒስትሮች ስለ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የነበራቸውን ትዝታ ገልጸዋል።
የቀድሞዋ የትምህርት ሚኒስትር አምባሳደር ገነት ዘውዴ (ዶ.ር) ዛሬ ከዚህ በመምጣቴ ደስ ብሎኛል ነው ያሉት። ኖሬ የዩኒቨርሲቲዎችን የትምህርት መስፋፋት በማየቴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ባለውለታዎችን በማመሥገኑ፣ በስማቸው ተቋም መሰየሙ እንደ ሀገር አዲስ ባሕል የፈጠረ ነው ብለዋል።
የአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ተማሪ መኾናቸውን የተናገሩት የቀደሞ ሚኒስትሯ ትምህርት ሀገርን ከድህነት ያወጣል፣ ልማት ያመጣል፣ ግለሰቦችን ደግሞ ራሳቸውን እንዲችሉ ያደርጋል ነው ያሉት። የትምህርት ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚያስደንቅ ሁኔታ ማደጉንም ተናግረዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትምህርትን ለማስፋፋት በነበረው ቁርጠኝነት የሠራው ሥራ ውጤት የታየበት እንደኾነም አስረድተዋል። ዩኒቨርሲቲው ውብ፣ ያማረ እና ታላቅ መኾኑን መመልከታቸውንም አመላክተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብቁ ተማሪዎችን እንደሚያወጣ እና የሚያወጣቸው ተማሪዎችም በራሳቸው የሚተማመኑ እንደሚኾኑም ያላቸውን ዕምነት ተናግረዋል።
የቀድሞው የትምህርት ሚኒስትር ስንታየሁ ወልደሚካኤል (ዶ.ር) የትምህርት ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የትምህርት ተሳትፎ፣ ጥራት፣ አግባብነት እና ተለማጅነት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚለውን መሠረት በማድረግ መሥራታቸውን ገልጸዋል።
ተሳትፎ ቢጨምርም የትምህርት ጥራት አልተረጋገጠም ነበር ያሉት የቀድሞው ሚኒስትር የትምህርትን ጥራት በአንደኛ ደረጃ እና በሁለተኛ ደረጃ ለማረጋገጥ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ነገር ግን በተፈለገው ልክ ማረጋገጥ አለመቻላቸውን ነው የተናገሩት። የትምህርት ተገቢነትን ለማረጋገጥ ጥረት ማድረጋቸውንም አንስተዋል። አሁንም ለትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ገልጸዋል። ትምህርት መጀመሪያ ራሳችንን መቀየር አለበት፣ ከዚያ አካባቢን እና ሀገርን መቀየር ይቻላል ነው ያሉት።
ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተነስተው የትምህርት ሚኒስትር መኾናቸውንም አስታውሰዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስኬቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳሰቡት የቀደሞው ሚኒስትር ይህን ማድረግ ከቻላችሁ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ የትምህርት መሠረት ይኾናል ነው ያሉት።
የቀድሞዋ የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ መግዘፉን እና መላቁን አንስተዋል። ማኀበራዊ አገልግሎቱም ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። እየሰጠው ያለው አገልግሎት ስኬታማ እና አርዓያ የሚኾን እንደኾነም ተናግረዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባሰብኩ ቁጥር በርካታ አካላትን ያቀፈ እና ያካተተ መኾኑ ያስገርመኛል ነው ያሉት። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከቀድሞው ተማሪዎች ጋር ያለው ግንኙነት የጠበቀ መኾኑንም ገልጸዋል። መልካሙን እያስቀጠለ መሄድ እንደሚገባውም አንስተዋል። ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚያደርገው ድጋፍ የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቃል ኪዳን ቤተሰብም የሚያስደንቅ መኾኑን ነው የገለጹት። የቃል ኪዳን ቤተሰቡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚያጠናክር፣ ብዙ ችግሮችን እንድናልፍ ያደረገን ነው ብለዋል። የትምህርት ሥርዓቱ እና ምርምሩ ዘመኑን የዋጀ መኾን እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
የዓለም ሁኔታ አይገመቴ እየኾነ መጥቷል ያሉት ፕሮፌሰሯ ይህን ግምት በማስገባት ተማሪዎችን፣ መምህራንን እና ተመራማሪዎችን ማዘጋጀት ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋ