
ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ “ከአጋር ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ማኅበር” ጋር በመተባበር በሰው የመነገድ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገር፣ ተዛማጅ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው ክልላዊ የትብብር ጥምረት የ2017 በጀት ዓመት ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ዓላማ ያደረገ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሄዷል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም በሰው የመነገድ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገር እና ተዛማጅ ወንጀሎች ዋነኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ናቸው ብለዋል።
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል እና ጉዳት ከደረሰ በኋላም በማከም ረገድ በጥምረት እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው በ2017 በጀት ዓመት በሕገ ወጥ መንገድ ሊዘዋወሩ ለነበሩ ከ11 ሺህ 880 በላይ ለኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሕይዎታቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን መታደግ መቻሉን አንስተዋል።
ከ100 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል።
በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር ሲያሻግሩ እና ሲደልሉ በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ደግሞ ለሕግ በማቅረብ ከ15 እስከ 20 ዓመት ድረስ በሚያቆይ እስር መቀጣታቸውን አንስተዋል። በቅንጅት ከተሠራ ሕገ ወጥ የሰዎችን ዝውውር መቀነስ ይቻላል ነው ያሉት።
የአጋር ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ማኅበር ፕሬዝዳንት አምባሳደር አበራ አደባ (ዶ.ር) በርካታ ግለሰቦች ሰውን አታልለው በመሸጥ ወንጀል ስለተሰማሩ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሀገር የሚፈልሱ ሰዎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሞት እየደረሰባቸው ነው ብለዋል።
የሕገ ወጥ የሰዎችን ዝውውርን እና ፍልሰትን ለመከላከልም በመጀመሪያ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ ከቦታ ቦታ እና ከሀገር ሀገር የሚንቀሳቀሱትን ሕጋዊ መንገድ ማቅለል አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመዋል።
በሕገ ወጥ የሰዎች ድለላ ሥራ ተሰማርተው ለሰዎች ቀቢጸ ተስፋ በመስጠት በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር በማሻገር እና ተዛማጅ ወንጀሎችን በሚፈጽሙት ላይ የሚወሰደው የሕግ እርምጃም አስተማሪ፣ የተጠናከረ እና ከፍተኛ መኾን አለበት ብለዋል።
የአማራ ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር እምዬ ገነቱ ሁሉም አጋር አካላት የየራሳቸውን የሥራ ድርሻ በመወጣት ሕገ ወጥ የሰዎችን ዝውውር በእጅጉ መቀነስ ይቻላል ነው ያሉት።
በፌዴሬሽኑ በሕጋዊ መንገድ ወደ ዓረብ ሀገር ለሚሄዱ እና ለሚመለሱ ሴቶች ግንዛቤ በመፍጠር እና ዕድሎችን በማመቻቸት ሊደርስባቸው ከሚችል ችግር መታደግ ተችሏል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የሥራ ሥምሪትና የሥራ ገበያ መረጃ ዳይሬክተር ጌታሰው አሞኜ የሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር መውጣት አስከፊ መኾኑን በማሳያዎች በማስደገፍ እናስተምራለን ነው ያሉት።
ጉዳዩን በአማራጭነት ለመከላከልም “ዜጎች ሠልጥነው፣ በቅተው እና ተወዳዳሪ ኾነው ወደ ውጭ እንዲሄዱም እየሠራን ነው ብለዋል።
ወንጀሎችን ለመከላከል በትብብር እየተሠራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በዚህ ዓመት ብቻ ከ6 ሺህ በላይ ዜጎች አካባቢያቸውን ለቅቀው ወደ ሌሎች ሀገራት ሊሄዱ ሲሉ በማኅበረሰቡ ጥቆማ እና በጸጥታ አካሉ ጥብቅ ክትትል ተይዘዋል ብለዋል። ለእነዚህ ዜጎችም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመሥጠት እና ወደ አካባቢያቸው በመመለስ የሥራ ዕድል በመፍጠር በሀገራቸው ላይ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደርጓል ነው ያሉት።
በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር የወጡ ዜጎች አላስፈላጊ መስዋዕት እየከፈሉ መኾናቸውን አንስተዋል። ዜጎች ሕጋዊውን አካሄድ እንዲከተሉ፣ ኅብረተሰቡም ሕገ ወጥ ፍልሰት አደገኛ በመኾኑ አጥብቆ እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!