ሕዝብ እንዳይጎዳ እና እንዳይበደል በማሰብ የሰላም አማራጭ መቀበሉን የቀድሞ ታጣቂ ቴዎድሮስ ከበደ ተናገረ።

41

ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር መተማ እና አካባቢው ታጥቆ ሲንቀሳቀስ የነበረው እና ራሱን የካራማራ ክፍለ ጦር ብሎ የሰየመው ቡድን የኮሙዩኒኬሽን እና የመረጃ ዕቅድ ትንተና መምሪያ ኀላፊ የቀድሞ ታጣቂ ቴዎድሮስ ከበደ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብሏል።

ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም ሊመጡ እንደሚገባ የቀድሞ ታጣቂ አቶ ቴዎድሮስ ከበደ ተናግሯል።

እየተስተዋለ ባለው የሰላም እጦት ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾናዋል፤ ማኅበረሰቡ በሰላም ወጥቶ መግባት ባለመቻሉ እና የልማት ሥራዎች እየተደናቀፉ በመኾኑ የሰላምን አማራጭ መከተል የግድ እንደሚልም ተናግሯል።

ከአካባቢውም ኾነ ከክልሉ ውጭ ኾነው ነገሩን የሚያባብሱ አካላት ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው ነው ያለው። የኢትዮጵያን እናት እንባ ለማበስ ጫካ ያሉ ጓዶች ወደ ሰላም በመመለስ ልማት ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባቸውም ጥሪ አቅርቧል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰለም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ደረሰ አዱኛ መገዳደል ያለመግባባቶች መጀመሪያ ሲኾን የግጭቶች ሁሉ መቋጫው ግን ለሕዝብ ሰላም ቅድሚያ በመስጠት ውይይት እና ሰላም ነው ብለዋል።

አለመግባባትን በውይይት፣ በመቀራረብ እና በንግግር ለመፍታት የተወሰደው ውሳኔ ተገቢ እንደኾነ ገልጸዋል። በዞኑ ከዚህ በፊት ከ900 በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰለም አማራጭን በመቀበል ወደ ሰላም መግባታቸውንም ተናግረዋል።

የሰላምን አማረጭ ያልመረጡ ሌሎች የታጠቁ ኃይሎችም ለማኅበራሰቡ ሰላም ሲሉ የሰላም ጥሪውን እንዲቀበሉ ማሳሰባቸውንም ከክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጣናነሽ ፪ ወደ ጣና ሐይቅ ለመግባት ዝግጁ ኾናለች።
Next articleበቅንጅት ከተሠራ ሕገ ወጥ የሰዎችን ዝውውር መቀነስ ይቻላል።