
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የዓለም የጡት ማጥባት ሳምንትን ምክንያት በማድረግ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች የጤና መምሪያ ኀላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ አጋር እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን ሳምንቱ ሲከበር ከዘመናዊነት ጋር እየተፈተነ ያለውን ጡት የማጥባት ተግባር ሰፊ ግንዛቤ የሚፈጠርበት መኾኑን አስታውቀዋል።
ሕጻናት እስከ 1ሺህ ቀናት የእናት ጡት መጥባት ይኖርባቸዋል ያሉት ምክትል ኀላፊው ይህንን ለማድረግ ከትዳር አጋር ጀምሮ ኹሉም የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ጡትን ይተካል በሚል በሕገ ወጥ መንገድ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ጠቁመዋል። ይሕንን ትውልድ ገዳይ ድርጊት መቆጣጠር፣ ግንዛቤ መፍጠር እና ርምጃ በመውሰድ ማሥተካከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ጡት በተገቢው መንገድ ማጥባት ያስፈለገው ለሕጻናት ዕድገት እና የትውልድ ሽግግርን ለማረጋገጥ እንደኾነም ነው የተናገሩት።
ሳምንቱ ሲከበር በየደረጃው ያሉትን አካላት በፓናል ውይይት፣ ሕገ ወጥነትን በመከላከል እና ግንዛቤዎችን በመፍጠር መኾን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ደጊቱ ኑሬ ልጃቸውን ጡት እያጠቡ እንደሚያሳድጉ ገልጸዋል።
ሕጻናት የእናት ጡት ካልጠቡ ለአካልም ኾነ ለሥነ ልቦና ችግር እንደሚዳረጉ ግንዛቤው እንዳላቸው ነው የተናገሩት። እናቶች ለሕጻናት ልጆቻቸው እስከ ሁለት ዓመት ድረስ የላም ወተትም ይኹን የፋብሪካ ምርቶችን መስጠት የለባቸውም ነው ያሉት።
ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመጡት የሥርዓተ ምግብ እና የሕጻናት ጤና አገልግሎት ባለሙያ አማረ ምናለ በማኀበረሰቡ ዘንድ ከዘመናዊነት ጋር በተያያዘ ጡት ያለማጥባት ዝንባሌዎች እንደሚታዩ ጠቁመዋል። ይህንንም ለመቅረፍ የግንዛቤ ፈጠራ እና የስርፀት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የጡት ማጥባትን በውጤታማነት ለመተግበር በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም አንስተዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን