ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የይነሳ ሦስቱ ቀበሌ ነዋሪዎች የአንድ ቀን ችግኝ ተከላ መርሐግብር አካሂደዋል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ደን በማልማት፣ ለማኅበረሰቡ ምቹ አካባቢ በመፍጠር እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የፖሊሲ ነጻነትን እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።
በዞኑ ከደን ጥቅሞችን ለማግኘት በርካታ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን እና ከሕዝቡ ጋር መግባባት እንደተፈጠረም ተናግረዋል።
ከችግኝ ማፍላት እስከ ተከላ ድረስ ኅብረተሰቡ እንዲሳተፍ መደረጉን እና ዛሬ በሁሉም ወረዳዎች ተከላ መደረጉን ዋና አሥተዳዳሪው ጠቅሰዋል።
የባሕር ዳር ዙሪያ ዋና አሥተዳዳሪ ተመስገን ደግአረገ በበኩላቸው የችግኝ ተከላ ከተጀመረ ሦስት ሳምንት መኾኑን እና የዛሬው የአንድ ቀን ተከላ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በወረዳው በ13 ቀበሌዎች እና በ16 የተከላ ቦታዎች መተከሉን ገልጸዋል። የቀበሌው ሕዝብ ወጥቶ ችግኝ መትከሉን ነው የተናገሩት።
ተፋሰስን መሠረት ያደረገ እና ለሰብል ምርት የማይኾን መሬት በስፋት እየተተከለ መኾኑንም ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡን እና አካባቢን ማዕከል ያደረገ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ መኾኑንም አንስተዋል።
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደሳለኝ አድማሴ ተከላው የደን ሽፋንን በማሳደግ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የልፍኝ በላቸው በችግኝ ተከላው የሴቶች ተሳትፎ ጉልህ መኾኑን ገልጸዋል። “ሴቶች በየአደረጃጀታቸው ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን እንዲጸድቁም የበኩላችን እናደርጋለን” ብለዋል።
የቀበሌው ነዋሪ ቄስ ስለሺ መዝገቡ የተተከለው ችግኝ እንዲጸድቅ ማኅበረሰቡ ዘበኛ በመቅጠር እንደሚያስጠብቀው ነው የተናገሩት። ከዚህ ቀደም የተተከለው ችግኝም ማኅበረሰቡ በጋራ እየተጠቀመበት መኾኑን ገልጸዋል።
ወጣት እናትነሽ ዓለሙ እንደተናገረችው የቀበሌው ወጣቶች ተደራጅተው ችግኝ በመትከል እና በመንከባከብ ላይ ተሠማርተዋል። ከባለፈው ዓመት ጀምሮም ችግኞቹ እንዲጸድቁ እየተንከባከቡ መኾኑን ተናግራለች።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን