በበጀት ዓመቱ ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ከሙስናና ብልሹ አሠራር ማዳን ተችሏል።

11

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት ለአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ማሩ ቸኮል በቅድመ ዝግጅት ምዕራፎች ዓመታዊ እቅድ አዘጋጅቶ ከፈፃሚ፣ አስፈፃሚ፣ አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ በማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የሚጠኑ ተቋማትን እና የሃብት አስመዝጋቢዎችን የመለየት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ዘጠኝ የሥልጠና ሞጁሎችን በማዘጋጀት ባለሙያዎችን የማሠልጠን ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

በተለዩ 10 ተቋማት ሙስናን ለመከላከል የተጋላጭነት ጥናቶች መከናወናቸውን ገልጸዋል። ተቋማት ከየራሳቸው ባህሪ አንፃር የመነሻ እቅድ እንዲያቅዱ በማድረግና የፀረ ሙስና ጥምረትን በመጠቀም የተሠራው ሥራ የተሻለ እንደነበር አብራርተዋል።

በሙስናና ብልሹ አሠራር ሊባክን የነበረውን ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን አስታውቀዋል። ለተቋሙ በደረሠው ጥቆማ መሠረት በማድረግ 29 ሕገወጥ የሠራተኛ ዝውውሮችን ማስቀረት ተችሏል ነው ያሉት።

ምክትል ኮሚሽነሩ እንደገለጹት በመሬት ነክ ጉዳዮች፣ በቀበሌ ቤቶችና ከጨረታና ከግዥ ጋር በተያያዙ ብልሹ አሠራሮችን ክትትል በማድረግ ሙስናን የመከላከል ሥራዎች ማከናወኑን ጠቅሰዋል።

ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በአካል የመከታተልና ድጋፍ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። በአፈጻጸማቸው መሠረት በደረጃ በመለየትም የውድድር መንፈስ እንዲፈጠር በማድረግ የማበረታታት ጥረቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

ሙስናን በመከላከል ትግሉ የአመራሩ ትኩረት ማነስ፣ የቅንጅታዊ አሠራር በሚፈለገው ደረጃ አለመኾን፣ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ አለመጽደቅ፣ የሰው ኀይል እጥረትና የደረጃ ማነስ ዋና ዋና ያጋጠሙ ችግሮች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

በወጣቶችና በሴቶች ላይ ሥነ ምግባርን መሠረት አድርጎ መሥራት፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ተኪ ትውልድ ለመገንባት፣ የአሠራር ሥርዓት ማጥናትና ማሻሻል እንዲኹም ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኾናቸው በሪፖርቱ ተመላክተዋል።

ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክልሉን ኢኮኖሚ የሚደግፉ ውጤታማ ሥራዎች ተሠርቷል፡፡
Next article‎ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ደጀን ከተማ ደረሰች።