
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በውይይቱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ሁሉንም ተግባራት አቀናጅተው ለመሥራት ጥረት ማድረጋቸው ለተመዘገበው ዘርፈ ብዙ ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
በቀጣይ ወራት ሁሉም መሪዎች እና ሕዝቡ በከፍተኛ ትጋት እና ቁርጠኝነት በየደረጃው በሚከናወኑ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ርብርብ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት።
የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች የሁሉንም አካል ቅንጅት የሚፈልጉ ናቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በጊዜ የለንም መንፈስ በየደረጃው የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማስፋት የተቀመጠው ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የክረምት ወቅት በርካታ ተግባራትን የምንፈጽምበት ነው ብለዋል።
“በመትከል ማንሠራራት”መርህ አሻራችንን የምናሳርፍበት፣ ለትውልድ የምናሽጋግርበት፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተጎዱ ቤቶችን በመጠገን ወገኖቻችንን ከችግር የምንታደግበት፣ ሕይዎትን ለመታደግ ደም የምንለግስበት ነው ብለዋል። ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!