እውነተኛ ዳኛ ካለ እንኳን ባላንጋራ ወንዝም ይረታል የሚል ብሂል ያለው ሕዝብ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

30

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕንጻ ዕድሳት፣ የማስፋፊያ እና የዲጂታላይዜሽን ሪፎርም ሥራዎችን እያስመረቀ ነው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ በለውጥ መንገድ ላይ እየተጓዘች እንደምትገኝ ገልጸዋል። አዲሱ መንገድ የጀመረችበትን ሰባተኛ ዓመታት በተለያዩ መርሐ ግብሮች ማክበራቸውንም ተናግረዋል።

ውኃውን ከእነ ዓሳው አጥፍቶ ከ ‘ሀ’ የሚጀምረውን ተደጋጋሚ የአብዮት መንገድ እንዳልመረጠችም አመላክተዋል። ይህን ያልመረጠችው ከጥቅሙ ኪሳራው በማመዘኑ ምክንያት እንደኾነም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አረሙን ከስንዴው በጥንቃቄ እና በአስተውሎት የሚለየውን የሪፎርም ጎዳና መርጣለች ብለዋል። ሪፎርም የነበሩትን ጥንካሬዎች አልቆ የሚያስቀጥል እና ክፍተቶችን የሚያርም መንገድ መኾኑንም ተናግረዋል። መንገዱ አብሮ መጓዝ የሚፈልግን ሁሉ የሚያስተናግድ መኾኑን ነው የገለጹት።

የሪፎርም በረከቶች ብዙ መኾናቸውን የባሕር ዳር ከተማን እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ማየት ብቻ በቂ መኾኑን ነው የተናገሩት። የሪፎርም መንገድ ጠመዝማዛ፣ አሰልች እና አድካሚ ቢኾንም በርካታ ሀገራዊ መሠረቶችን አንጾ ለቀጣይ ትውልድ ዕዳን ሳይኾን ምንዳን የሚያወርስ ነው ብለዋል።

የለውጡ መንገድ በርካታ ሪፎርሞችን በአንድ ጊዜ ለመፈጸም እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። ከተያዙ ሪፎርሞች መካከል የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም አንደኛው መኾኑንም ገልጸዋል። የመንግሥት አገልግሎት ሪፎርም እና አሥተዳደር ሪፎርም የዘመናት ቋጠሮዎችን የምንፈታበት፣ የሕዝብን ርካታ ለመጨመር የሚያስችል ነው ብለዋል።

የዛሬ 100 ዓመት ሕዝባችን ጉዳይ ለማስፈጸም ደጅ ይጠና ነበር ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ100 ዓመት በኋላ ይህ ምን ያክል ተቀይሯል ብሎ የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ምላሽ መስጠት ይገባዋል ነው ያሉት። የአንድ ማዕከል አገልግሎት ምላሽ እየሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥራ ከባቢ እድሳት የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ውጤት ነው ብለዋል። ከዓመታት በፊት በፍርድ ቤቱ ያረጁ እና ያፈጁ መዝገቦች ተኮልኩለው የሚታይበት እንደነበር አስታውሰዋል።

የችሎት መሠረተ ልማቶች እና የአሠራር ሥርዓቶች ኋላቀር እና ሁሉም ነገር በሰው ልጅ ብቻ የሚከውን ነበር ነው ያሉት። በፍርድ ቤቱ አሁን ላይ የሥራ ከባቢ ማማር ብቻ ሳይኾን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት የተዘረጋለት ተቋም ነው ብለዋል። የፍርድ ቤቱ ለውጥ ሌሎቹ የክልሉ ተቋማት በምሳሌነት የሚወሰድ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ተቋማቱ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። እስከታችኛው መዋቅር ድረስ አሠራር መዘርጋት እንደሚገባም አመላክተዋል። በቂ ዝግጅት ተደርጎ ያልተገነባ ተቋም ዘመን ተሻጋሪ እና የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም እንደማይችል አንስተዋል።

ጠንካራ ተቋም ጠንካራ ሥርዓት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም ነው የለውጡ መንግሥት ለተቋም ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራው ብለዋል። ‘ፍርድ የሚሰጥበት ቦታ እና እህል የሚቀመጥበት ጎታ’ ከፍ ማለት አለባቸው ለሚል ሕዝብ ዛሬ የተመረቀው ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም ነው ያሉት።

ፍርድ ቤቱ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸው ሥራዎች በርካታ መኾናቸውን ገልጸዋል። የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል። በዳኝነት እና በፍትሕ ሥርዓቱ በርካታ ሥራዎች ቢሠሩም አሁንም መፍታት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አንስተዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ ለፍትሕ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እውነተኛ ዳኛ ካለ እንኳን ባላንጋራ ወንዝም ይረታል የሚል ብሂል ያለው ሕዝብ መኾኑን ተናግረዋል።

ከሁሉም በላይ “እህል ካለበት ሀገር ይልቅ ዳኝነት ካለበት ሀገር ሄደህ ኑር የሚል ሕዝብ ነው” ብለዋል። አባባሎቹ ሕዝብ ለፍትሕ ያለውን ክብር እና ፍቅር የሚያሳዩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። እንዲህ ባለ ሕዝብ መካከል ፍትሕ እና ርትዕ ካልሰፈነ የት ሊሰፍን ነው? እንዲህ ባለ ሕዝብ መካከል በጡንቻ የሚያምን አጉራ ጠናኝ ሊበቅል እንዴት ቻለ? የገበሬውን ከብት የሚነዳ፣ እህሉን የሚጭን፣ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር የሚዘርፍ ጉድ ከየት መጣብን? ጥናት ይፈልጋል ነው ያሉት።

“ዕውቀት ይስፋ፣ ድንቁርና ይጥፋ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች በዚህ ክልል ነበር የፈለቁት፣ ዕውቀት ይጥፋ፣ ድንቁር እና ይስፋ የሚሉ ጉደኞች ከየት ነው የመጡበት? ትውልድ ይሄን በአግባቡ ከመረመረ በፍርድ ቤቱ የተሠራው ሥራ በሌሎችን ተዳርሶ ክልሉ የዕድገት እና የብልጽግና ማዕከል ይኾናል ብለዋል።

የዛሬው የምረቃ ሥነ ሥርዓት አንድ ሕንጻ ከመመረቅ በላይ መኾኑንም ተናግረዋል። የፍትሕ ሥርዓቱን መልሶ ለመገንባት መሠረት የተጣለበት እንደኾነ ነው ያነሱት። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ኾነው ለውጥ ላመጡ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

ተቋሙን አይተህ መሪውን ተመልከት እንደተባለ የፍርድ ቤቱ ሥራም ያን ያሳየ መኾኑን ተናግረዋል። ክልሉ ካለበት ችግር በአንጻራዊነት እንዲወጣ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

መሪዎች ያሰቡትን እና ያቀዱትን ለመፈጸም በሥነ ምግባር መሥራት እንደሚገባቸው አንስተዋል። የአማራ ክልል ምቹ ከባቢ መፍጠሩ ለመዳራሻ ግቡ መነሻ እንጂ መዳረሻ እንዳልኾነ አንስተዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መነሻውን እንዳሳመረ ገልጸዋል። መዳረሻቸውን እንዲያሳምርም አሳስበዋል። መዳረሻቸው ላይ ለመድረስ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።

ለፍርድ ቤቱ ሥራ መሳካት ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱ የጀመራቸውን ሥራዎችን በመደገፍ፣ በክልሉ ፍትሕን፣ ሰላምን እና የሕግ የበላይነትን ለማጽናት ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፍርድ ቤቶችን መደገፍ ሕዝብን መደገፍ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“በመትከል ማንሠራራት ጉዞ ላይ ነን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ