“ፍርድ ቤቶችን መደገፍ ሕዝብን መደገፍ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

18

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕንጻ ዕድሳት፣ የማስፋፊያ እና የዲጂታላይዜሽን ሪፎርም ሥራዎችን እያስመረቀ ነው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሦስት አንኳር ጉዳዮችን በጋራ ለመሥራት መወሰናቸውን አስታውሰዋል። ቀዳሚው የተቋም ግንባታ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የተቋም ግንባታውን በደረጃ በመለየት መሠራቱን ገልጸዋል። ሕዝብ ለሚፈልገው የፍትሕ ሥርዓት እውን መኾን የሰው ኃይሉ ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራታቸውንም ተናግረዋል። የተቋማት አደረጃጀትም ሌላው ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

የዳኝነት ሥርዓቱ በሂደቱም ኾነ በውጤቱ የሕግ የበላይነቱን እንዲያረጋግጥ በሚያስችል ሁኔታ ማስኬድ የትኩረት መስክ እንደነበር አንስተዋል። በክልሉ የሕግ የበላይነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቶ ቆይቷል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ተቋምን ማሻሻል አንደኛው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሂደት መኾኑን ተናግረዋል።

የላቀ የፍትሕ አገልግሎት መስጠት ሌላኛው የትኩረት መስክ እንደነበርም ገልጸዋል። በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተሠሩ ሥራዎች ፍርድ ቤቱ እና የዳኝነት ሥርዓቱ ከነበረበት ችግር ለማስወጣት የሚያስችሉ መኾናቸውን አንስተዋል።

በተቋሙ አላሠራ ያሉ ማነቆዎችን ማሻሻል መቻሉንም ተናግረዋል። ውብ እና ጽዱ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። ምቹ የማስቻያ ቦታዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል።

ለዳኝነት እና ለፍትሕ ሥርዓቱ መቃናት የሚያግዙ ሥራዎች እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ሦሥቱ የመንግሥት አካላት በቅንጅት እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤት ማጠናከሪያ አዋጅ፣ የሕግ ማሠልጠኛ ማቋቋሚያ አዋጅ እና የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ በዚህ ዓመት መውጣታቸውን አስታውሰዋል። የዳኝነት ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያስችል የዲጂታላይዜሽን ሥራ ተሠርቷልም ነው ያሉት።

የዳኝነት ሥርዓቱ ማነቆ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሠራቸው ሥራዎች ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ናቸው ብለዋል። የክልሉ መንግሥት መሠረታዊ የለውጥ ሥራዎችን መሥራቱንም ተናግረዋል።

የክልሉን የወደፊት የመልማት እና የዕድገት ጸጋ ታሳቢ ያደረገ የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕቅድ መታቀዱንም አንስተዋል። በ25 ዓመታት ዕቅዱ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓቱ ያለውን አስተዋጽኦ ታሳቢ በማድረግ በዕቅዱ መካተቱን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ የተቋም እና የሥርዓት ግንባታ ላይ ጉልህ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል።

የዳኝነትን ነጻነት እና ገለልተኛነት ለማስጠበቅ ሥራዎች መሠራታቸውንም አንስተዋል። “በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተጀመሩ ሥራዎች እንደመነሻ የሚያገለግሉ እና ፍርድ ቤቱ ለያዘው ራዕይ መንደርደሪያ የሚኾኑ ናቸው” ብለዋል።

የምናገለግለው ሕዝብ በብዙ ችግር ውስጥ ያለ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል ልናገለግለው እና ልንክሰው ይገባል ነው ያሉት።

ለሕዝብ የዳኝነት እና የፍትሕ ተደራሽነት፣ የውሳኔ ጥራት እንዲኖር እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ማድረግ የቀጣይ የትኩረት ማዕከል መኾኑንም ተናግረዋል። ሁሉም የለውጥ ሥራዎች ፍትሕ እና ሥርዓትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መኾን አለባቸው ነው ያሉት። ፍርድ ቤቶችን መደገፍ ከውጤቱ ተጠቃሚ የሚኾነውን ሕዝብ መደገፍም ነው ብለዋል።

ክልሉ ያለበትን ችግር ተቋቁመው በተገኘው መልካም ውጤት ላይ ለተሳተፉ ሁሉ ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት። ድጋፍ ላደረጉ ሁሉም ምሥጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋ

Previous article“በግልጽ ችሎት መዳኘት ሕግ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የዜጎች መብት ነው” አቶ ቴዎድሮስ ምህረት
Next articleእውነተኛ ዳኛ ካለ እንኳን ባላንጋራ ወንዝም ይረታል የሚል ብሂል ያለው ሕዝብ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ