“ሁለት ቤተሰብ የሚደግስላችሁ ተማሪዎች ዕድለኞች ናችሁ” አሥራት አጸደወይን (ዶ.ር)

24

ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ.ር) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሰኔ 30/1949 ዓ.ም ተማሪዎችን ማስመረቅ መጀመሩን አስታውሰዋል። ባለፉት 70 ዓመታት የተማረ ትውልድ እያፈራ መምጣቱን ገልጸዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በየዘመናቱ ከፍ እያለ መምጣቱን ገልጸዋል። ዛሬ 2 ሺህ 599 ተማሪዎች እየተመረቁ መኾናቸውን ተናግረዋል። ዛሬ የተመረቁ ተማሪዎችን ከዓመታት በፊት ወላጆቻቸው ሲልኩልን እጁን ዘርግቶ የተቀበለልን የጎንደር ሕዝብ ነው ብለዋል።

ከአንደኛው ቤታቸው እና ከቤተሰብ ርቀው ለመጡ ሁሉ ሁለተኛ ቤት እና ሁለተኛ ቤተሰብ ኾኖ በቃል ኪዳን ልጄ ብሎ እንደተቀበላቸው አስታውሰዋል። ሁለት ቤተሰብ የሚደግስላችሁ ተማሪዎች ዕድለኞች ናችሁ ብለዋል። ከአራቱም አቅጣጫ የመጡ ልጆችህን በፍጹም ኢትዮጵያዊ ፍቅር እያስመረቅህ ያለኸው የጎንደር ሕዝብ ምስጋና ይገባሃል ነው ያሉት።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዛሬዎችን ሳይጨምር ከ107 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እንዳስመረቀ አስታውሰዋል። የዛሬው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በማኅበረሰብ አገልግሎት በልሕቀት ላይ ነው ብለዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በምርምር ልቆ የሚታይ ሥራ መሥራቱንም ገልጸዋል። ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመራቃችሁ ሁሉ ኩራት እንደሚሰማችሁ አልጠራጠርም ነው ያሉት።

በአካላዊ እና ስነልቦናዊ በሽታ ለሚሰቃዩ ወገኖች፣ ምርጥ ዘር እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለሚፈልጉ ገበሬዎች፣ የባለሙያ ድጋፍ አጥተው ለተቸገሩ ወገኖች፣ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ ለሚመኙ ተማሪዎች፣ ሥራ ማግኘት ሕልማቸው ለኾኑ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በምርምር የታገዘ ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲውን 70 እና የሆስፒታሉን 100 ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ 22 ፕሮጄክቶችን ማስመረቃቻውን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ እንዲኖረው የተጀመረው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

በዛሬው የምረቃ ሥነ ሥርዓት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተከፈተው በኦኮፔሽናል ቴራፒ የሠለጠኑ የበኩር እጩ መኖራቸው ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።

ተመራቂዎች ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሲወጡ ተመልሰው ቤታቸውን እንደሚደግፉ እና ቃል ኪዳናቸውን እንደሚጠብቁ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በሚኖሩበት አካባቢ እና በሚሠሩበት ተቋም የተማሩበትን ዩኒቨርሲቲ እና የተማሩበትን ማኅበረሰብ የላቀ ስምና ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ ሕዝብ እንዲያገለግሉ አደራ ብለዋል።

ሥራ ፈጣሪ እንጂ ሥራ ጠባቂ እንዳይኾኑም አሳስበዋል። ሕዝባችንን ለመካስ፣ የእናት ሀገራችን እንባዋን ለማበስ፣ ቋጠሮዎቿን ለመፍታት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጣቸውም ተመኝተውላቸዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ኪን ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት” የመጀመሪያ ጉዞ ወደ ቻይና ሊደረግ ነው።
Next articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎችን በድጋሜ አስመረቀ።