የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የተጀመረው ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

32

ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም ፋራህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ላለፉት ሦስት ቀናት የተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ያከናወኗቸውን ተግባራት በጥልቅ መገምገማቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማሻገር የሚያስችል አቅምን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዳበርን እንደመጣን፣ በአባል እና በመሪዎቻችን የጋራ ጥረት ዓመቱን ስኬታማ ያደረጉ ድሎችን ማሳካታችን ገምግመናል ነው ያሉት።

በመትከል የማንሰራራት ግብን በመያዝም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኞችን መተከላቸውን ተናግረዋል።

በድሬዳዋ ከተማ ከመደመር መጽሐፍ ገቢ የተሠራውን የእመርታ ቤተ መጻሕፍት፣ የድሬዳዋ ከተማ የኮሪደር ልማትን፣ የድሬ ስቲል የብረታ ብረት ፋብሪካ፣ አማ የምግብ ዘይት ማቀነባበሪያ ድርጅትን፣ በሕዝብ፣ በመንግሥት እና በግል ባለሀብቶች ቅንጅት የተሠሩ የልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል።

ከፓርቲ ሥራዎች ግምገማ ባሻገር በ2017 በጀት ዓመት በፓርቲና መንግሥት ቅንጅት በንቅናቄ ተግባራዊ ሲደረጉ የነበሩ ከተረጂነት የመላቀቅ፣ የኑሮ ውድነትን የማቃለል እና የክህሎት መር የሥራ እድል ፈጠራ አፈጻጸምን ገምግመው የቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጣቸውን አስታውቀዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል፣ እርምት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ በማድረግ የጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ግብን ለማሳካት እና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የጀመርነውን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበየዓመቱ ችግኝ በመተከሉ የዛሮታ ወንዝ እየጠነከረ መጥቷል።
Next article118 ፕሮጀክቶችን እየገነባ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን እና አካበቢው አልማ ጽሕፈት አስታወቀ።