ምክር ቤቱ የተሻሻለውን የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ አጸደቀ።

74

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጽድቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለተኛ አስቸኳይ ስብሰባው፤ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በነባሩ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም በፖለቲካ ፓርቲዎች አሥተዳደር፣ በምርጫ እና በምርጫ ስነ ምግባር የባለድርሻ አካላት መብትና ግዴታ ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ የሚያስችል ድንጋጌዎችን ያካተተ መኾኑን አስረድተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመውሰድ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጥርጣሬ እና ሥጋትን በማስወገድ ጊዜ እና ወጪን ሊቆጠብ በሚችል ዘመናዊ አሠራር ለመተግበር የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በፊት የታዩ እና ወደፊትም ሊከሰቱ ይችላሉ ተብሎ የሚገመቱ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒነት ያለው የምርጫ ሂደት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን እና ወጣቶችን በምርጫ ለመሳተፍ እድል የሚፈጥር እና በምርጫ ሂደት የሚነሱ ቅሬታዎችን በተገቢው መንገድ ለመፍታት የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት ረቂቅ አዋጁ መሻሻሉ ለቀጣይ ለሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ የዲሞክራሲአዊ ሥርዓትን ለመገንባት አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው አንድ ጠንካራ ድርጅት መፍጠር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡


በኢትዮጵያ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲጎለብት እና የዲሞክራሲ ባሕል እንዲዳብር በግልፅ የተገኙ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በረቂቅ አዋጁ መመላከት እንዳለባቸው የተፎካካሪ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት አስገንዝበዋል፡፡

ምክር ቤቱ፤ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1394/2017 አድርጎ በሁለት ተቃውሞ፤ በአራት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleለዋግ ኽምራ የአረንጓዴ አሻራ የውዴታ ግዴታ ነው።
Next articleየተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ አስፈላጊው ክትትል ይደረጋል።