በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የተከሏቸውን ችግኞች እንደሚንከባከቡ በደቡብ ወሎ ዞን የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

15

ደሴ፡ ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ፈጠቆማ ቀበሌ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት የችግኝ የተከላ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

የቀበሌው አርሶ አደሮች አካባቢያቸው ከዚህ ቀደም ድርቅ የሚያጠቃው እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ግን በተፋሰስ ልማት አካባቢያቸውን መቀየር መቻላቸውን አንስተዋል።

በቀጣይም የተተከሉ ችግኞችን እንደሚንከባከቡ ለአሚኮ ተናግረዋል።

የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም እንድሪስ በዚህ ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 2 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል። ከዚህ ውስጥም 20 በመቶ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መኾናቸውን ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አህመድ ጋሎ ለአረንጓዴ አሻራ ሥራው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል።

ዞናዊ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐግብርም ተካሂዶ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች ተከላ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ከተከላ ቦታ ልየታ አኳያ 29ሺህ 675 ሄክታር መሬት ላይ የደን እና የአግሮፎረስትሪ ችግኞችን ለመትከል እና ከ19ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ሌሎች ችግኞችን ለመትከል ቦታ መለየቱን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ 211 ሚሊዮን የደን እና የአግሮ ፎረስትሪ ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ ከ206 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን መምሪያ ኀላፊው ጠቁመዋል። ከዚህ ውስጥ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የሚኾነው የፍራፍሬ ችግኝ እንደኾነም ተናግረዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ሰላም ወሳኝነት ያለው በመኾኑ የዞኑን ሰላም ለማስጠበቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።

አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማስጠበቅ ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብሩ የክልል እና የዞኑ ከፍተኛ መሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎችም ተሳታፊ ኾነዋል።

ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleክረምት እና መብራት።
Next articleየሥነ ልቦና ጉዳት እና መፍትሔው፦