
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን አሁን ከከተሞች መስፋፋት እና ከዘመናዊነት ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ ኀይል ከየዕለት ኑሯችን ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ኾኗል፡፡ ከትንንሽ አምራቾች እስከ ኢንዱስትሪዎች፣ ከቤት ውስጥ የማብሰል ተግባራት እስከ ባለኮኮብ ሆቴሎች ድረስ ኤሌክትሪክ የመጠቀም ባሕል ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ ይሁን እንጅ ለቤት ውስጥ ግልጋሎት እና ለገቢ ማስገኛ ሥራዎች ጥቅም ላይ የሚውል ኤሌክትሪክ የኃይል የመቆራረጥ ችግር ሲያጋጥመው ይስተዋላል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ በጸጉር ሥራ፣ በልብስ ስፌት፣ በኤሌክትሮኒክስ ጥገና፣ በብረት ብየዳ፣ በዳቦና ኬክ መጋገሪያዎች፣ በካፌና ሬስቶራንቶች፣ በግሮሰሪዎች እና መሰል ሥራዎች የተሰማሩ ዜጎች ሥራቸው በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ የተመሠረተ በመኾኑ በተደጋጋሚ ኤሌክትሪክ በሚቋረጥበት ጊዜ እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡
የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላቸው በጀኔሬተር ይሠራሉ፤ የማይችሉት ደግሞ መብራት እስኪመጣ ሥራቸውን አቁመው ይቆያሉ፡፡ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችም ቢኾን የዚህ ችግር ሰለባ ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ በክረምት ወቅት ችግሩ ይደጋገማል፡፡ በዚህ በክረምት ወቅት ዝናብ ሲዘንብ መብራት እንደሚጠፋ ተገማችና አብዛኛውን ጊዜ የሚስተዋል ነገር ነው፡፡
ለመሆኑ በክረምት ወቅት በተደጋጋሚ መብራት የሚጠፋው ለምንድን ነው?
የመብራት መቆራረጡ ችግር ክረምቱ ከገባ ወዲህ የበለጠ እየተባባሰ መምጣቱን የነገሩን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ ታዘበ ከፊያለው ናቸው። ዝናብ በመጣ ቁጥር የመብራት መጥፋት ችግር በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥም ገልጸዋል።
ይህ ችግርም የኀይል መጨመርን እና መቀነስን በመፍጠር በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ላይ ጉዳት ያደርሳል፤ የሚመለከተው ተቋምም ትክክለኛ የኀይል አቅርቦት እንዲኖር ኀላፊነት ወስዶ መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት። ችግሮች ሲያጋጥሙ መብራት ኀይል በአካልም ኾነ በስልክ ለሚቀርብለት ጥያቄ ፈጣን አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባሕር ዳር ሪጅን ዲስትሪክት ኔትወርክ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሽመላሽ ግርማው እንደገለጹት መብራት የሚጠፉው በሥሦት ዋና ዋና ምክንያቶች መኾኑን ገልጸውልናል፡፡
የመጀመሪያው በክልሉ ውስጥ ያሉ የኀይል ማከፋፈያ ከአቅም በላይ መሸከም ነው። ይህም የኤሌክትሪክ ኀይል በፈረቃ እንዲሠሩ የሚያደርግ እና የተጠቃሚዎችን ሥራ የሚያስተጓጉል መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ረጃጅም ዛፎች ከኤሌክትሪክ መስመሮች ጋር እርጥበት እና ንክኪ ሲኖር በሚፈጠሩ ችግሮች የሚመጣ የኀይል መቆራረጥ ችግር ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንድ አካባቢ ላይ የሚፈጠር ችግር አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሲስተሙን ያስተጓጉላል ነው ያሉት፡፡ በተለይም በምዕራብ አማራ ዛፎች ቶሎ የሚያድጉ እና በጣም ረጃጅም ከመኾናቸው የተነሳ በዝናብ እና በነፋስ ኀይል ከኤሌክትሪክ መስመሮች ጋር ሲነካኩ ችግር ይፈጥራሉ ነው ያሉት፡፡
ሌላው ምክንያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት እና ዘረፋ ነው ይላሉ፡፡ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቱን ለመዝረፍ ሲባል ባዕድ ነገሮችን መስመሮች ላይ በመጨመር ኀይል እንዲቋረጥ እየተደረገ ስርቆት ይፈጸማል ብለዋል፡፡ ተግባሩ በጨለማ የሚፈጸም በመኾኑ በሚቋረጥበት ጊዜ ፈትሾ ችግሩን ለመፍታት አስቻጋሪ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
መብራት በዝናብ መምጣት ምክንያት ኾን ተብሎ አይጠፋም ያሉት ኀላፊው ነገር ግን በዝናብ ጊዜ በነፋስ ኀይል ዛፎች ከኤሌክትሪክ መስመሮች ጋር ንክኪ ሲፈጠር በእርጥበቱ ምክንያት ኤሌክትሪክ ወደ መሬት ይፈሳል፤ በዚህ ጊዜ በመስመሩ ላይ ከፍተኛ የኾነ የኤሌክትሪክ ፍሰት ይኖራል፤ የኀይል መቆጣጠሪያዎች ከትክክለኛ ሁኔታ ውጭ የኾነ ችግር መስመሮች ላይ ሲኖር ከሰው ንከኪ ነጻ ኾኖ በራሱ እንደሚዘጋ ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ ጊዜ ይህንን የሚቆጣጠረው ሰው ኀይል ለመልቀቅ አይሞከርም ምክንያቱም ያለውን የዝናብ፣ ነፋስ እና ሌሎች ምክንያት የሚኾኑ ጉዳዮች እስከሚረጋጉ ይጠበቃል፤ በዚህም ኀይል ይቋረጣል ነው ያሉት፡፡
ዝናቡ እና ነፋሱ ከቆመ በኋላ ኀይል ለመልቀቅ ይሞከራል መስመሮች ላይ ችግር ከሌለ ወደ ነበረበት ይመለሳል። ካልኾነ ግን ድጋሚ መቆጣጠሪያው ይመልሳል፤ ይህ ደግሞ በምሽት የሚኾን ከኾነ ችግሩ የተፈጠረበት ቦታ ፈትሾ ለማግኘት እና ለማስተካከል አስቸጋሪ ስለሚኾን መብራት ጠፍቶ የሚያድርበት ሁኔታ ይፈጠራል ነው ያሉት፡፡
ችግሮችን የሚለዩ እና የሚፈቱ 24 ሰዓታት አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። በተጠቀሱት ምክንያቶች በሚፈጠሩ ችግሮች እንጅ ገና ዝናብ ችግር ይፈጥራል ተብሎ ኀይል አይቋረጥም ነው ያሉት፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ምክንያታቸውን የመመዝብ ሥራ ተሰርቶ ሰባ በመቶ የሚኾነው ችግር የኤሌክትሪክ ከመስመር ወደ መሬት መፈሰስ መኾኑ መረጋገጡንም ነው የጠቆሙት።
ለዚህም ከመስመሮች ጋር ንክኪ ያላቸው ዛፎች እየተቆረጡ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ በአረጁ መስመሮች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቀድሞ ለመፍታት የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት ምሰሶ በመቀየር በሚሠሩ ሥራዎች ውጤት እየታየ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የኀይል ማሰራጫው ከአቅም በላይ መሸከም የሚስተካከለው የኀይል ማሰራጫዎችን ግንባታ እና አቅም በማሳደግ ሲኾን በረጅም ጊዜ የሚፈታ እና እንደ ሀገር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ሊሠራው የሚችል መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ኅብረተሰቡም በተቻለ አቅም ከኤሌክትሪክ መስመር አካባቢ ያሉ ዛፎችን እንዲቆርጡ፣ አጫጭር ዛፎችን እንዲተክሉ እና በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ስርቆትን ለመከላከል ሁሉም አካል ጥበቃ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ እንደተቋምም ችግሮችን ለመፍታት ከፍትሕ አካላት ጋር በጋራ ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን