የዜጎች ጤና እና ማኅበራዊ ደኅንነት እንዲጠበቅ እየተሠራ ነው።

10

አዲስ አበባ: ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስቴር ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ውይይት እያካሄደ ነው። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ወደ ምርጫ ክልላቸው ሲመለሱ አንኳር የጤና ሥራዎችን ይዘው ሊኾን ይገባል ብለዋል። በ2018 በጀት ዓመት ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ቀርበው በውይይቱ የሚነሱ ሀሳቦች የእቅድ ግብዓት እንደሚኾኑም ጠቁመዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕል እና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ ባለፉት አራት ዓመታት የምክር ቤት አባላቱ በጤናው ዘርፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል። ለአብነትም የጤናው ፖሊሲ መሻሻልን አንስተዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ምክር ቤቱ ከጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የዜጎች ጤና እና የሕዝቦች ማኅበራዊ ደኅንነት እንዲጠበቅ እየተሠራ ነው ብለዋል። አባላቱ ወደ ታች ወርደው ሕዝቡ በጤና ተቋማት የሚያገኘውን አገልግሎት እና ክፍተቶች በመረጃ እና ማስረጃ መከታተል አለባቸውም ብለዋል። ይህም ጤናው የተጠበቀ ዜጋን ለመፍጠር እንደሚያስችል ነው ያነሱት።

በ2017 በጀት ዓመት የእናቶችን ሞት በመቀነስ፣ በሥርዓተ ምግብ፣ በሽታን በመከላከል እና መቆጣጠርን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ለአባላቱ ገለጻ አድርገዋል።

ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመከላከያ ሠራዊት ከግዳጅ ባሻገር በችግኝ ተከላ የካበተ ልምድ እንዳለው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
Next articleክረምት እና መብራት።