
አዲስ አበባ: ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 7ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት በመላ ሀገሪቱ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ሥራ መጀመሩ ይታወሳል። ተቋማትም በዚህ መርሐ ግብር መሳተፋቸውን ቀጥለዋል። ዛሬ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄን በመምሪያው ዋና ግቢ አስጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መከላከያ ሠራዊት እንደተቋም ከግዳጅ ባሻገር በችግኝ ተከላ የካበተ ልምድ እንዳለው ገልጸዋል። ችግኝ በመትከል የሚታዩ ለውጦችን ማስመዝገቡንም ተናግረዋል። አሁንም እንደሀገር እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በልምዱ እያገዘ ቀጥሏል ብለዋል።
እንደመከላከያ ተቋም በዚህ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 18 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታስቧል ያሉት ፊልድ ማርሻሉ ለዚህ ስኬት በመከላከያ ውስጥ ካሉ ግቢዎች ባሻገር ተለይተው በተሰጡት ቦታዎች ላይ በየግዳጅ ቀጣናው ባሉ የሠራዊቱ አባላት ይፈጸማል ብለዋል። ከአረንጓዴ አሻራ ባሻገር የዘንድሮው የበጎ ፈቃድ ተግባርም እንደ ተቋም “ከካምፓችን ወደ ሕዝባችን” በሚል መሪ መልዕክት መጀመሩንም የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ አንስተዋል። ሁሉም የሠራዊቱ አባላት በተለመደ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ በንቃት መሳተፋቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!