ሕጻናት የተስተካከለ አካላዊ እና አዕምሮአዊ ዕድገት እንዲኖራቸው ጤናማ የአመጋገብ ዘዴ ጉልህ ድርሻ አለው።

5

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎‎ለአንዲት ሀገር እድገት ንቁ ጠንካራ፣ ጤነኛ እና ተመራማሪ የኾነ ዜጋ ወሳኝ ነው።

ይህ የሚፈጠረው ደግሞ ከልጅነት ጀምሮ በሚሠራ ሥራ እንደኾነ ቻይልድ ፍሎሪሽድ የተሰኘ በልጆች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ድርጅት ያጠናው ጥናት ይገልጻል።

ሀገራት የዕድገታቸው ቁልፍ ለኾነው ትውልድ የማስቀጠል ሥራ ከመቸውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ። በተለይም ልጆች ተወልደው ሁለት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ የሚሰጡት ትኩረት ልዩ ነው።

ነገ ተመራማሪ እና የሀገር ዋልታ የኾነ ዜጋ ለማግኘት ይህ ጊዜ ወሳኝ እንደኾነ በማመን ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ።

ለመኾኑ ኢትዮጵያውያን እናቶች ይህን እንዴት ይረዱት ይኾን?

ወይዘሮ መሠረት አዱኛ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እና የአራት ልጆች እናት ናቸው። ወይዘሮዋ ልጅ በእድሉ ይደግ እና ልጅ ሆዱ ከሞላ ከማለት ውጭ ትኩረት እንደሚፈልግ ግንዛቤ ከሌላቸው እናቶች መካከል ነበሩ።

ይሁን እንጅ ዘመኑ ሲዘምን እና ስለልጆች ያለው ትኩረት በጤና ተቋማት ሲጨምር እሳቸውም በጤና ባለሙያዎች ምክር አማካኝነት ዕውቀታቸውን ከፍ እያደረጉ ልጆቻቸውን ማሳደግ እንደቻሉም ነው የሚናገሩት።

ወይዘሮ መሠረት አራተኛ ልጃቸውን እንደፀነሡ ከጽንስ ጀምሮ ክትትል እንዳደረጉ እና ለልጃቸውም እስከ 6 ወራት ካጠቡ በኋላ ተጨማሪ የልጆች ምግብ እንደጀመሩለት ገልጸዋል። በዚህ የአመጋገብ ሥርዓታቸው ልጃቸው ፈጣን እና ጤናማ እንደኾነም አስረድተዋል።

ሌላኛዋ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ቤቴልሔም ያረጋል የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው። ወይዘሮ ቤቴልሔም ምንም እንኳን የልጆች እንክብካቤ ላይ የነበረው አስተሳሰብ ክፍተት እንደነበረበት አንስተዋል። አሁን ላይ ግን የሕጻናት አመጋገብ እና እንክብካቤ ላይ የነበረው ግንዛቤ እየተስተካከለ መጥቷል ነው ያሉት።

ወይዘሮ ቤቴልሔም አሁን ላይ ከእርግዝናቸው ጀምሮ ለልጃቸው የተለያዩ እንክብካቤዎችን እያደረጉ እንዳሉ ነግረውናል። ከጤና ባለሞያዎች ጋር በመነጋገርም ከተለያየ የእህል ዘር ምጥን በማዘጋጀት ከስድስት ወራት በኋላ ለልጃቸው እንደሚመግቡ ገልጸዋል።

በባሕርዳር ዩኒቨርስቲ የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕጻናት ስፔሻሊስት ዶክተር አላምረው አለባቸው እንዳሉት የመጀመሪያወቹ 1ሺህ ቀናት ከእርግዝና የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ያለውን የሰው ልጅ የሕይወት ዑደት ያጠቃልላል።

ሕጻናት የተስተካከለ አካላዊ እና አዕምሮአዊ ዕድገት እንዲኖራቸው ጤናማ የአመጋገብ ዘዴ ጉልህ ድርሻ አለው ይላሉ፡፡ ይህ ጤናማ የአመጋገብ ዘዴ ልጆቹን ከተለያዩ በሽታዎች እንደ ተቅማጥ፣ የሳምባ ምች፣ የጀሮ ‘ኢንፌክሽን’ እና ሌሎችንም ተላላፊ በሽታዎች በመከላከል ከፍተኛ የኾነ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የተናገሩት።

እንደ ዶክተሩ ማብራሪያ ከእርግዝና ጀምሮ በእነዚህ 1ሺህ ቀናት የሚደረጉ እንክብካቤወች እና የአመጋገብ ሁኔታዎች በሕጻናቱ አጠቃላይ የሰውነት እና የአዕምሮ እድገት ላይ ወሳኝ ተጽዕኖ ያሳርፋሉ።

እነዚህ ቀናት የአካላዊ፣ የአዕምሮአዊ እና የማኅበራዊ ክህሎት ዕድገት የሚመዘገብበት እና የቀጣይ ሕይወታቸው መሠረት የሚጣልበት ወሳኝ የሕይወት ምዕራፍ በመሆኑ ትኩረት የሚሰጠው እንደኾነ ነው የጠቆሙት።

በእነዚህ 1ሺህ ቀናት ዉስጥ አስፈላጊ ከኾኑ ነገሮች መካከል ወላጆች የቅድመ እርግዝና ክትትል በማድረግ የጤናቸውን ሁኔታ ማወቅ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል። እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ኤች አይ እና መሰል የጤና ሁኔታዎችን ማወቅ እንደሚገባ ነው ያስረዱት።

እናቶች በርግዝና ወቅት የሚያስፈልጓቸውን እንደ ፎሊክ አሲድ እና አይረን መጀመር እንዳለባቸው፣ ጤናማ እና ገንቢ ምግቦችን መመገብ፣ በቂ የኾነ የርግዝና ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው አብራርተዋል።

በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ሕጻናት ያለምንም ተጨማሪ ምግብ የእናት ጡት ብቻ በቀን ከስምንት እስከ 12 ጊዜ እንዲወስዱ ይመከራል፡፡

እንደ ዶክተር አላምረው አለባቸው ገለጻ ጨቅላ ሕጻናት ወዲያው በተወለዱ በ30 ደቂቃ ውስጥ የእናት ጡት መጀመር አለባቸው፡፡ በተለምዶ በተለይ በገጠራማው አካባቢ ጨቅላ ሕጻናት ወዲያው እንደተወለዱ ከእናት ጡት በፊት የሚሰጡ እንደ አብሽ፣ ቅቤ፣ ሻይ፣ ውኃ በስኳር የመሳሰሉትን መስጠት ለኢንፌክሽን ስለሚያጋልጣቸው ጎጂ ልምድ ነው ብለዋል፡፡

ከስድስት ወር ጀምሮ ግን ማንኛውም ሕጻን የተመጣጠነ ጤናማ ምግብ መመገብ፤ ወላጆች በቂ የኾነ የተመጣጠነ ምግብ እና እንክብካቤ ለልጆቻቸው መስጠት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከተሟሉ ብቁ ምርታማ እና ጥራት ያለው ትውልድ ማፍራት እንደሚቻልም ነው የጠቆሙት።

ብቁ፣ ምርታማ እና ጥራት ያለው ትውልድ ለማፍራት በእነዚህ ቀናት ውስጥ በየደረጃው በወላጆች፣ በጤና በባለሙያዎች እና በሚመለከታቸው አካል ትኩረት ተሠጥቶ መሥራት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሴቶች ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በእንክብካቤ ላይም እንዲሳተፉ እየተሠራ ነው።
Next articleዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።