አልማ በማኅበራዊ ልማት ዘርፎች ያከናወናቸውን ተግባራት የሚያሳይ የፎቶ ኤግዚቪሽን ለዕይታ አቀረበ፡፡

13

ደብረማርቆስ፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎‎የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባለፉት አምስት ዓመታት በማኅበራዊ ልማት ዘርፎች ያከናወናቸውን ተግባራት የሚያሳይ የፎቶ ኤግዚቪሽን ለዕይታ አቅርቧል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን አልማ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉ ጥጋቡ ሕዝቡ በራሱ ባዋጣው ሀብት የተገነቡ የትምህርት፣ የጤና፣ የሥራ ዕድል እና መሰል ጉዳዮች ላይ የተከናወኑ ተግባራትን በፎቶ ለዕይታ ማቅረባቸው ተናግረዋል።

የፎቶ ኢግዚቢሽን ማኅበረሰቡ በራሱ የመልማት አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት ግንዛቤ የሚፈጥር መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የልማት ማኅበሩ በዞኑ ከ655 ሺህ በላይ አባላትን በማቀፍ በመንግሥት አቅም ሊሸፈኑ የማይችሉ የማኅበራዊ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መኾኑንም አብራርተዋል።

በቀጣይ ከአባላት እና ከአጋር አካላት ሰፊ ሀብት በመሠብሠብ የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ ለመፍታት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ ማኅበሩ የመንግሥትን ክፍተት በመሙላት ማኅበረሰቡ የሚገለገልባቸውን የትምህርት፣ የጤና እና መሰል ልማቶች የውስጥ አቅማቸውን በማሳደግ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ትልቅ ሚና እየተወጣ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በጸጥታ ችግሩ የተጎዱ ተቋማትን በመጠገን እና አዳዲስ የኅብረተሰብ ጥያቄዎችን ተቀብሎ እንዲፈታ ዞኑ በጋራ ይሠራል ብለዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተወካይ ከንቲባ አስምሮም ሞስነህ አልማ በከተማው የትምህርት ቤቶችን እና የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሳደግ ምቹ የትምህርት እና የጤና አገልግሎትን እያረጋገጠ ነው ብለዋል።

የከተማው ማኅበረሰብ ለአልማ እያደረገ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ መኾኑን የጠቆሙት ተወካይ ከንቲባው የልማት ማኅበሩ የሚያከናውነው ተግባር ሕዝብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተጨባጭ የሚያስመሰክር መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አልማ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ አየነው መኮነን አልማ ከሕዝብ እየሠበሠበ ለሕዝብ የሚሠራ ሕዝባዊ ተቋም መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ከአባላት በማሠባሠብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደግ እና ለሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች የመስሪያ ሸዶችን ገንብቶ ለማስረከብ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ከ2017 ዓ.ም እስከ 2021 ዓ.ም የሚተገበር ዕቅድ በማዘጋጀትም 191 ሚሊዮን ብር በመሠብሠብ ሕዝብን ያሳተፈ ልማት ለማከናወን ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

”የአልማ ሳምንት” መርሐግብር በዞኑ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረም ይገኛል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
Next articleበትምህርት ቤቶች የደረጃ ማሻሻል ሥራ ላይ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጠየቀ።