የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

46

ጎንደር፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎‎በማዕከላዊ ጎንደር ዞን “ጥንካሬዎቻችን በማስቀጠል እና ጉድለቶቻችንን በማረም ወደ ሁለንተናዊ ስኬት እናመራለን” በሚል መሪ መልዕክት ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
‎
‎በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አማካሪ ግዛት አብዩ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን ገልጸዋል። ተፈጥሮ በቆየው የጸጥታ ችግር ምክንያት
ከማኅበረሰቡ ባሕል እና እሴት የወጡ ኢ ሰብአዊ ድርጊቶች መፈጸማቸውን አንስተዋል። ይህንንም ማውገዝ እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የድርሻን መወጣት ይገባል ብለዋል።
‎
‎መድረኩ የሃይማኖት አባቶች ለሀገር ሰላም የነበራቸውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግን ዓላማ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
‎
‎የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ሰላም እንዲሰፍን ውይይት ቀዳሚው መፍትሔ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
‎
‎በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ያነሱት አሥተዳዳሪው
አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል።
‎
‎የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም የነበራቸው ሚና ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። ላደረጉት አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበዋል።
‎
‎ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ እሴትን መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።
‎
‎የጸጥታ ችግሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች እያስከተለ መኾኑም ተገልጿል።
‎
‎በመድረኩ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በዞኑ የጸጥታውን ችግር ተከትሎ የተከሰቱ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል። የጸጥታ ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝም የበኩላቸውን እያበረከቱ መኾኑን ተናግረዋል።
‎
‎መንግሥትም ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል። ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
‎
‎ታጥቀው የወጡ አካላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ለማድረግ ረገድ እየሠሩ መኾናቸውን ተገልጿል።
‎
‎በዞኑ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ከ600ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸው ተነስቷል። በመሠረተ ልማቶች፣ በጤና ተቋማት እና በሌሎችም አገልግሎቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማስከተሉም ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ ‎ቃልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleዛሬ የለገስነው ደም ነገ ለእኛም ነው።
Next articleአልማ በማኅበራዊ ልማት ዘርፎች ያከናወናቸውን ተግባራት የሚያሳይ የፎቶ ኤግዚቪሽን ለዕይታ አቀረበ፡፡