ዛሬ የለገስነው ደም ነገ ለእኛም ነው።

10

ደብረ ታቦር: ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ደም በመለገስ ሕይወትን ያድኑ” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የክረምት በጎ ፈቃድ አካል የኾነው የደም ልገሳ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው የበጎ ፈቃድ ደም በመለገስ ሕይወትን መታደግ ትልቅ የህሊና ርካታ እንደሚሰጥም ነው የተናገሩት። ደም የመለገስ ተግባር የሁልጊዜ ተግባር መኾን እንዳለበትም አክለዋል።

ከዚህ በፊት የደም እጥረት ያጋጥም እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ በረከት ገደፋው ናቸው። በየጊዜው የሚሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ማኅበረሰቡ በደም ልገሳ ተሳትፎ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዳለው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በደም ምክንያት ሪፈር የሚባሉ ታካሚዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ በረከት አሁን ላይ በወጣቶች እና በማኅበረሰቡ ባለው የደም ልገሳ ንቅናቄ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ኀይለ ኢየሱስ ሰለሞን ደም መለገስ አንዱ የፍቅር መገለጫ ነው ብለዋል።

በበጎፈቃደኛ ወጣቶች እና ማኅበረሰቡ የሚለገስ ደም ብዙ ሕይወትን ያተርፋል ነው ያሉት።

የበጎ ፈቃድ ተግባራት በደም ልገሳ ብቻ ሳይኾን የአቅመ ደካማ ቤቶችን በማደስ እና በአረንጓዴ አሻራ ጭምር የማኅበረሰቡ ተሳትፎ የጎላ እንደኾነ ተናግረዋል። ይህ ተግባርም ለቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ ኀይለ ኢየሱስ አሳስበዋል።

“የምንለግሰው ደም ነገ ለእኛም ነው” ያሉት የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ወርቁ ያየህ ዛሬ ላይ የሚለገሰው ደም በተለያየ ምክንያት ደም በማጣት ሕይወታቸውን የሚያጡ ወላድ እናቶች እና ሌሎችን የሚያተርፍ ነው ብለዋል።

ደም የመለገስ ተግባር የክረምት በጎ ፈቃድን ብቻ ጠብቆ የሚሠራ ተግባር ሳይኾን በየሦስት ወሩ መለገስ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት የደንበኞችን ርካታ ለማረጋገጥ ይሠራል።
Next articleየሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።