ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት “ኸልዚ ሴኪዩሪቲ አክቲቪቲ” የተባለ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት የክልሉን ሕዝብ የጤና ሥርዓት ለማሻሻል በክልሉ አቅም እና በተለያዩ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እየተሠራ ይገኛል።
ዛሬ የተጀመረው ፕሮጀክትም በክልሉ የተመረጡ 56 ወረዳዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ፕሮጀክቱ በክልሉ ማኅበረሰብ ላይ በወረርሽን መልክ ሊከሰት የሚችልን በሽታ መለየት እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዝግጁነት እና ምላሽን ማጠናከር ላይ ኩረት አድርጎ ይሠራል። የላቦራቶሪ ምርመራን ማጠናከር በተለይም ደግሞ መድኃኒት የተላመዱ ጀርሞችን ለመለየት የላቦራቶሪዎችን የመመርመር አቅም መገንባት ላይ ትኩረት አድርጎም የሠራል ብለዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ እንዳሉት በክልሉ የማኅበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ እና ለማሻሻል ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል። ዛሬ የተጀመረው መርሐ ግብር የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብሩን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርግ መኾኑን ጠቁመዋል። ዘላቂ የጤና ሥራዎችን ተደራሽነት እና ፍትሐዊነት ለማሳደግም ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
የ”ኸልዝ ሴኪዩሪቲ አክቲቪቲ” ፕሮጀክት ምክትል ኀላፊ ኤሊያስ ዋለልኝ ፕሮጀክቱ የሰው፣ እንስሳት እና የአካባቢ ጤና ሥርዓት ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ የማኅበረሰብ አቀፍ በሽታ ክትትል፣ በጦርነትም ኾነ በተለያየ መንገድ የተጎዱ ላቦራቶሪዎችን መልሶ ማቋቋም፣ የሰው ኀይሉን መደገፍ፣ የጸረ ተህዋሲያን መላመድን የመመርመር አቅም ማጎልበት ሌላኛው የትኩረት መስክ መኾኑንም ገልጸዋል። በጤና ዘርፍ ከሚያስተምሩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ፕሮጀክቱ የማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል ወደ ክልሉ በመምጣቱ አመስግነዋል። ፕሮጀክቱ በቀጣይ ለሚያከናውነው ሥራም ክልሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በክልሉ በተከሰተው ግጭት በጤና ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን አንስተዋል። ተቋማትን ወደ ተሟላ አገልግሎት ለመመለስ አጋር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!