
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የውኃ ወለድ በሽታዎች በዓለማችን ላይ ዋነኛ የጤና ችግሮች ከኾኑ በሽታዎች መካከል ይጠቀሳሉ። በተለይም የንጽሕና አጠባበቅ እና የውኃ ማጣሪያ ሥርዓት ባልተሟላባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የኅብረተሰብ ጤና ስጋት ይፈጥራሉ።
ወይዘሮ ብርቱካን ሞላ ይባላሉ፡፡ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ በመንግሥት ሥራ ተቀጥረው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በሚሠሩበት አካባቢ የውኃ እጥረት በመኖሩ በቅርብ ከሚገኝ ምንጭ ውኃ በመቅዳት ለተለያዩ አገልግሎቶች ይጠቀሙ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከጊዜ በኋላም ከፍተኛ የኾነ ተቅማጥ፣ ትውከት እና የማቅለሽለሽ ስሜት እንደተሰማቸው ይናገራሉ፡፡ ትኩሳቱም ከፍተኛ ስለነበር ወደ ሕክምና በመሄድ ምርመራ ሲያደርጉ የኮሌራ በሽታ መያዛቸው ነው የተነገራቸው፡፡
ወይዘሮ ብርቱካን አስፈላጊውን የሕክምና ክትትል በማድረግ እንደተሻላቸው እና ከዛን ጊዜ ጀምሮ ውኃውን በማፍላት እና በውኃ አጋር በማከም እየተጠቀሙ ጤናቸውን እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የዋሽ እና አካባቢ ጤና አጠባበቅ አስተባባሪ መከተ አድማስ እንደገለጹት እነዚህ በሽታዎች የሚተላለፉት በበሽታ አምጭ ተህዋስያን በተበከለ ውኃ አማካኝነት ነው።
የውኃ ወለድ በሽታ እንዴት ይከሰታል?
የውኃ ወለድ በሽታዎች የሚከሰቱት በተለያዩ ምክንያቶች ነው ይላሉ አስተባባሪው።
ከእነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ፦
👉 ለመጠጥ፣ ለምግብ ማብሰያ እና ለንጽሕና አጠባበቅ ያልታከመ ውኃ መጠቀም
👉 ትክክለኛ የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴዎች አለመኖር እና በጥንቃቄ ያልተያዘ የመጸዳጃ ቤት
👉 ከፍተኛ የኾነ የሕዝብ ቁጥር ባለበት በቂ ንጽሕናው የተጠበቀ ውኃ አለመኖር
👉 ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ የውኃ ምንጮችን በቆሻሻ ፍሳሽ እና በካይ ነገሮች እንዲበከሉ ሲያደርጉ
👉 የታከመ እና ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ወይም ተደራሽነት አለመኖር
👉 ንጽሕናቸው ባልተጠበቀ እና ክፍት በኾነ ኮንቴይነር ውስጥ ውኃ ማጠራቀም
👉 በቂ ያልኾነ የእጅ መታጠብ ልማዶች በሽታ አምጭ ተህዋስያንን ሊያስተላልፉ ይችላሉ
👉 የሰው እና የእንስሳት ዐይነ ምድር፣ ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ፈሳሾች ውኃውን በባክቴሪያ፣ ቫይረስ፣ ፕሮቶዞዋ፣ ፓራሳይት (ጥገኛ ተዋህስያን) እና ፈንገሶች እንዲበክል ያደርጋሉ።
👉 አንድ ሰው ይህን የተበከለ ውኃ ሲጠጣ፣ በተበከለ ውኃ የታጠቡ ምግቦችን ሲመገብ፣ በተበከለ ውኃ ውስጥ ሲዋኝ ወይም ገላውን ሲታጠብ፣ በሽታ አምጭ ተህዋስያኑ ወደ ሰውነት ውስጥ በመግባት የውኃ ወለድ በሽታ እንዲከሰት ያደርጋሉ ነው የሚሉት።
በውኃ ወለድ በሽታ የተያዘ ሰው ከሚያሳያቸው የተለመዱ ምልክቶች መካከል:-
👉 ተቅማጥ፣
👉 ትኩሳት፣
👉 የሆድ ቁርጠት፣
👉ድካም፣
👉ማስታወክ፣
👉የሆድ ድርቀት (ከባድ ተቅማጥ እና ማስታወክ በሚኖርበት ጊዜ) እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።
የተለያዩ የውኃ ወለድ ተህዋስያን በርካታ በሽታዎችን ያስከትላሉ። ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹ:-
👉 ኮሌራ፣
👉 ታይፎይድ፣
👉 ሄፓታይተስ ኤ፣
👉 ተቅማጥ (አጣዳፊ የውኃ ተቅማጥ)፣
👉 ትራኮማ (የዓይን በሽታ)፣
👉 የቆዳ ቁስል፣
👉 ታይፈስ፣
👉 እከክ፣
👉 ቢልሀርዚያ (ስኪስቶሶሚያሲስ)፣
👉 ጊኒ ወርም (ድራኩንኩሊያሲስ)፣
👉 ወባ (በተለይ ወባ ትንኝ በመራቢያ ስፍራዋ ውኃ ስለምትፈልግ) እንደሚገኙበት ነው ያብራሩት።
የውኃ ወለድ በሽታዎችን እንዴት መከላከል ይቻላል?
የውኃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል ንጹሕ እና በቂ ውኃ ለማኅበረሰቡ እንዲደርስ የልማት ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። ንጹሕ ውኃ እንዳይበከል ጥንቃቄ ማድረግ በሽታውን ለመቆጣጠር እንደሚያግዝም ገልጸዋል። የውኃ ማከሚያ ዘዴዎች መጠቀም በሽታውን ለመከላከል እንደሚጠቅም የተናገሩት አስተባባሪው የግል ንጽሕናን በተለይም ምግብ ከማዘጋጀት፣ ከመመገብ በፊት፣ ከመጸዳጃ ቤት በኋላ እጅን በሳሙና እና በንጹሕ ውኃ መታጠብ ያስፈልጋል ብለዋል። የውኃ ወለድ በሽታን በወቅቱ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ በክሊኒካል ምርመራ እና በላብራቶሪ ውጤት ማወቅ እና ተገቢውን ሕክምና ማግኘት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን