ያለ አሽከርካሪ የሚጓዘው መኪና!

32

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ይህ አዲሱ ሞዴል መኪና፣ ቴስላ ግዙፍ ፋብሪካው ከሚገኝበት ኦስቲን ቴክሳስ ተነስቶ ምንም አይነት አሽከርካሪ ሰው ሳያስፈልገው፣ ግዥውን የፈጸሙ ደንበኞች ወደ ሚገኙበት ሕንጻ ድረስ በራሱ ተጉዞ ለባለቤቶቹ ተላልፏል።

ይህ ክንውን ቴስላ ሙሉ በሙሉ በራስ የመንዳት ቴክኖሎጂ ያለውን እድገት በግልጽ የሚያሳይ ነው። የቴስላ መስራቹ እና ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢሎን መስክ ኩባንያው ለመጀመሪያ ጊዜ ዋይ የተሰኘ አዲስ ሞዴል መኪናውን ያለ ሹፌር ለደንበኛው አስረክቧል።

መስክ በኤክስ ማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባጋራው ቪዲዮ መኪናው ከፋብሪካው ተነስቶ ወደ መዳረሻው ሕንጻ ለመድረስ ያለፈባቸውን ሂደቶች አሳይቷል፡፡ መኪናው ምንም ሰው የጫነም አልነበረም።

ይህ ራስገዝ (Autonomus) መኪና ያለምንም አሽከርካሪ በተቀመጠለት መንገድ ለመጓዝ የሴንሰሮች፣ የካሜራዎች፣ የጂ.ፒ.ኤስ፣ የራዳር እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ሥርዓትን በጥምረት የሚጠቀም ነው።

እንደ ቴክታርጌት ድረ ገጽ መረጃ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች ለመንገድ ትራንስፖርት እና ለመጓጓዣ ኢንዱስትሪዎች ብዙ ለውጦችን የማምጣት አቅም አላቸው።

የትራፊክ መጨናነቅን በመቀነስ፣ የአደጋዎችን ቁጥር በመቀነስ እና የጭነት አገልግሎቶችን በማሳለጥ ጉልህ ሚናን መጫወት ይችላሉ፡፡

ከቴስላ ባሻገር ቢ.ኤም.ደብሊው፣ ፎርድ፣ ጉግል እና ቮልስዋገንም አሽከርካሪ አልባ መኪናዎችን ለማምረት እና ወደ ሥራ ለማስገባት እየሞከሩ ያሉ ኩባንያዎች መኾናቸውን ቴክታርጌት አስነብቧል፡፡

እነዚህ የመኪና ሥርዓቶች የሚሠሩት በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ነው። ለውጤታማነቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ምስል መለያ (image recognition) ሥርዓቶችን፣ የማለማመድ ሂደቶችን እና የነርቭ አውታር መረብ ሥልተ ቀመርን (Neural Network) ይጠቀማሉ።

የአሽከርካሪ አልባ መኪና ሥርዓቶች ውስጥ ያሉ ሴንሰሮች የትራፊክ መብራቶችን፣ ዛፎችን፣ መንገዶችን፣ እግረኞችን፣ የመንገድ ምልክቶችን እና ሌሎችንም ከባቢያዊ ነገሮች ለመለየት ኒውራል ኔትወርኩ የሚጠቀምበትን መረጃ ጭምር ይሰበስባሉ።

በመኪናው በዙሪያ ያለውን ነገር ለመረዳት የአካባቢውን ካርታ ያዘጋጃል ከዛም መንገዱን ያቅዳል፡፡ የትራፊክ ደንቦችን በመከተል እና መሰናክሎችን በማስወገድ ወደ መዳረሻው ለመድረስ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ፈጣን መንገዶችን ይወስናል።

ምንጭ፡-
cnbc.com
techtarget.com

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleከ114 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።
Next articleከስደት ተመላሾችን ሕይወት ለማሻሻል የተቀናጀ እና የተደራጀ የቅብብሎሽ ሥርዓትን መከተል ይገባል።