
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ስሚሽንግ በሌላ ስሙ የስልክ መልዕክት ማስገር ጥቃት ይባላል፡፡ የሳይበር ጥቃት አድራሾች የማኅበራዊ ምሕንድስና ጥቃት ስልቶችን በመጠቀም በሚልኳቸው የስልክ መልዕክቶች ሰዎች የግል ምሥጢራዊ መረጃቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ የሚያደርጉበት የማጭበርበሪያ ስልት ነው፡፡
የማኅበራዊ ምሕንድስና ጥቃት የሚባለው መረጃ መንታፊዎች ሰዎችን በማግባባት፣ በማታለል እና በጥቅም በማማለል ለሳይበር ጥቃት የሚያጋልጡ የግል መረጃዎችን የሚያገኙበት የጥቃት ዓይነት ነው፡፡ ጥቃት አድራሾች በስልክ የሚልኳቸው መልዕክቶች ከባንክ እና ታማኝ የትስስር ገጾች እንደተላኩ በማስመሰል የሚልኳቸው ናቸው፡፡ ይዘታቸው ደግሞ ኢላማ የተደረጉ አካላት በፍጥነት ለመልዕክቶቹ ምላሽ እንዲሰጡ የሥነ ልቦና ጫና የሚፈጥሩ እና የተላኩ ማሥፈንጠሪያዎችን በመከተል የግል መረጃቸውን እንዲያጋሩ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ጥቃት አድራሾቹ የሚልኳቸው መልዕክቶች ከመደበኛ የስልክ መልዕክት ባለፈ በዋትስአፕ፣ በቴሌግራም፣ ቫይበር እና መሰል በይነ መረብ ተጠቃሚ የመልዕክት አማራጮችን ጭምር በመታገዝ ነው፡፡ ሂደቱ የሚጀምረው በሚላኩ የጥቃት መልዕክቶች ነው፡፡ ኢላማ ተደርገው መልዕክቱ የደረሳቸው ሰዎች አገልግሎት ከሚያገኙባቸው ባንኮች ወይም ሌላ ተቋማት እንደተላከላቸው እና በአስቸኳይ ምላሽ የሚሻ በማስመሰል ጥድፊያ እና ወከባ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ ነው፡፡ ከመልዕክቱ ጋር ተጣምሮ ተጠቂዎች በሚላክላቸው ስልክ አሊያም ማስፈንጠሪያ በመደወል እና ወደ ተላከ ገጽ በመግባት ምሥጢራዊ መረጃዎችን በመላክ ሰለባ ይኾናሉ፡፡
ምሥጢራዊ መረጃ የሚባሉት ኢላማ የተደረጉ ግለሰቦች እና ተቋማት የሚጠቀሙባቸው ሙሉ ስሞች፣ የትውልድ ቀን፣ የሚወዷቸው እና የሚያዘወትሯቸው ነገሮች፣ ኢ-ሜይሎች፣ የይለፍ ቃሎች፣ የባንክ እና የገንዘብ ተቋማት መገልገያ ቁልፎችን ያካትታል፡፡
የራሱን የባንክ ይለፍ ቃል አሳልፎ ለእነዚህ የሳይበር ጥቃት አድራሾች ያጋራ ሰው ወይም ተቋም የገንዘብ ኪሳራ ሊደርስበት እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ የስሚሽንግን ጥቃትን (በስልክ በሚላክ መልዕክት የሚፈጸም የጥቃት አይነት) ለመከላከል ወሳኝ ከሚባሉት መፍትሔዎች ውስጥ የሚላኩ ሊንኮችን ምንጭ እርግጠኛ ሳንኾን አለመንካት፣ ለአጠራጣሪ የስልክ መልዕክቶች ምላሽ አለመስጠት፣ ምንጩን ለማናውቀው የስልክ ጥሪ የግል መረጃ አለማጋራት እና የመሳሰሉ ጥንቃቄዎችን ማድረግን ያካትታል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!