አማራጭ አቅሞችን ተጠቅሞ ክልሉን ከችግሮቹ ማላቀቅ ወቅቱ የሚጠይቀው የአመራር ጥበብ ነው።

14

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ የ25 ዓመት የልማት እና የእድገት ፍኖተ ካርታ ዙሪያ ሥልጠና እየወሰዱ ነው። በሥልጠናው የክልሉ ሁለንተናዊ ችግሮች፣ አቅሞች፣ የመልማት እድሎች እና አማራጮች በጥልቀት ውይይት እየተደረገባቸው ነው።

የሥልጠናው ተሳታፊዎች ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ችግሮችን ከነመፍትሄዎቻቸው የሚያመላክት፣ ቁጭት እና መነሳሳት እንዲሁም አቅም የሚፈጥር መኾኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አማካሪ ተስፋሁን ተሰማ እቅዱ በርካታ ምሁራን የተሳተፉበት እና በቁጭት የተዘጋጀ መኾኑንም ገልጸዋል።

የክልሉን የመልማት አቅም ግምት ውስጥ ያስገባ፣ በስፋት እና በጥልቀት የዳሰሰ እና የወደፊቱን ተስፋ ያካተተ መኾኑንም አንስተዋል።

በሥልጠናው ለአሁኑ ብቻ ሳይኾን ለቀጣይ ትውልድም ምን መሠራት እንዳለበት በጥልቀት እየታየ መኾኑን አንስተዋል።

ዕቅዱ ክልሉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲኾን የሚያስችል እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም መሥራት እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝብ መኾኑንም ገልጸዋል።

አመራሩ ራሱን አብቅቶ ለወደፊቱ የልማት ደረጃ እንዲዘጋጅ የሚያደርግ ነው። ትውልድን ታሳቢ ያደረገ እና ለሀገርም ለክልልም አሻጋሪ የኾነ ሥራ መሥራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በቀጣይ የ5 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድም ክልሉን ከገጠሙት ችግሮች በማውጣት ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ በድጋሚ የድህነት እና የግጭት አዙሪቶች ውስጥ ላለመግባት ሰፊ ሥራ መሥራት የሚያስችል መኾኑን አንስተዋል። የመካከለኛ ጊዜ እቅድን ግብ በማሳካት ቀጣዩ ትውልድ ለ25 ዓመቱ እቅድ አሻራውን እንዲያበረክት መሠረት የሚጥል መኾኑን አንስተዋል።

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን የተዘጋጀው የ25 ዓመት እቅድ የክልሉን የወደፊት መዳረሻ የሚያመላክት መኾኑን ገልጸዋል።

በርካታ ዘርፎችን የያዘ እና ሽግግር ያለው፣ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚፈጸም ጥልቅ እቅድ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

እስካሁን ያልታዩ ሃብት እና አቅሞችን ያመላከተ፣ የእስካሁን እቅድ እና አፈጻጸምን የዳሰሰ፣ በቀጣይስ እንዴት እንደሚፈጸም ጥልቅ ግምገማ የተደረገበት እና አመራሮች ራሳቸውን እንዲጠይቁ ያደረገ መኾኑንም አንስተዋል።

ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወደፊት ለመሄድ በሚደረግ ጥረት ሁሉም ተቋም ያለውን አቅም፣ የሚያስፈልገውን ሃብት እና የኅብረተሰቡን አስተዋጽኦ አካትቶ በማቀድ ክልሉን ከችግር የሚያወጣ አፈጻጸም እንደሚኖረው ገልጸዋል።

አማራ ክልል በርካታ የመልማት አቅሞች እንዳሉት የጠቀሱት አቶ አታላይ ይህንን አቅም አመራሩን፣ የየደረጃውን ፈጻሚ አካል እና ኅብረተሰቡን አዋህዶ ለውጤት ማብቃት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል ምክትል ኀላፊ የሺ ካሴ አማራ ክልል በርካታ ሃብት እና ዕውቀት እንዲሁም ታታሪ ሕዝብ ያለው ቢኾንም ለምን ድህነትን እና ግጭትን መሻገር እንደቸገረው ውይይት እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።

ከአመራሩ እስከ ኅብረተሰቡ ድረስ ቁጭት በመፍጠር ችግሮችን ለመፍታት፤ አመራሩን በማነቃነቅ ወደ ሥራ የሚያስገባ እቅድ መኾኑንም ገልጸዋል።

እቅዱ በርካታ ምሁራን ተወያይተው ያዘጋጁት እና ከፍተኛ አመራሮችም ችግሮችን በጥልቀት ተወያይተው ክልሉን ከችግር ለማውጣት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

አመራሮች በእቅዱ ላይ መሠልጠናቸው በቀጣይ በቁጭት እንዲሠሩ ያስችላል ብለዋል።

እቅዱን ለመፈጸም ቁርጠኛ መኾን ለአመራሩ የፍላጎት እና የምርጫ ጉዳይ ሳይኾን ግዴታ መኾኑን ያነሱት ወይዘሮ የሺ ችግሮችን ለመቅረፍ በቁርጠኝነት እንሠራለን ብለዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ንጹህ ሽፈራው ሥልጠናው ክልላችን በግጭት ውስጥ ያለፈ፣ ድህነት እና ሥራ አጥነት የሚፈትነውም በመኾኑ በለውጥ አስተሳሰብ በተዘጋጀ እቅድ ላይ እየተወያየን ነው ብለዋል።

ክልሉ ከግጭት እና ችግር ያልወጣበትን ምክንያት፣ ለሀገር ያለውን አበርክቶ በማየት ያለውን ሃብት እና ጸጋ ያማከለ የ25 ዓመት የዕድገት እና ልማት እቅድ ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

እቅዱ በቁጭት የተዘጋጀ እና በውይይት ለመተግበር ዝግጅት የተደረገበት መኾኑን አንስተው ክልሉን ካለበት ችግር የሚያወጣ፣ ሥራ አጥነት እና ድህነትን የሚቀርፍ፣ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ለትውልዱ የተሻለ ነገር የሚያመጣ መኾኑንም ገልጸዋል።

በሥልጠናው ራሳችንን እና ክልላችንን ፈትሸን እንድናውቅ እና በርካታ ሃብት እያለን ለምን በዚህ ደረጃ ተገኘን ብለን እንድንቆጭ አድርጎናል ብለዋል። አመራሩም ሠርቶ ውጤት እንዲያመጣ የሚገፋፋ መኾኑን አንስተዋል።

ወይዘሮ ንጹህ እቅዱ ያላየነውን እና የማናውቀውን ሃብት እና እድሎች እንድናይ ያደርጋል ብለዋል። በየቢሯችን ያልሠራናቸውን ሥራዎች እንድንፈትሽ እና የ25 ዓመቱን እቅድ የሚያሳካ የ5 ዓመት ዕቅድ እንድናዘጋጅ ያስችለናል፤ ለዚህም አስቀድመን የምናቅድበትን አሠራር አበጅተናል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ስፖርት በሁሉም መንገድ የነቃ ማኅበረሰብ ለመፍጠር አስፈላጊ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleአማራጭ አቅሞችን ተጠቅሞ ክልሉን ከችግሮቹ ማላቀቅ ወቅቱ የሚጠይቀው የአመራር ጥበብ ነው።