
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ራንሰምዌር በተቋማት፣ በቁልፍ የመሠረተ ልማት አውታሮች እና በግለሰቦች ላይ ታልሞ የሚፈጸም የሳይበር ጥቃት ዓይነት እና ለከባድ ኪሳራ የሚዳርግ ነው፡፡ ጥቃቱ ኮምፒውተሮችን በመበከል እና በመቆለፍ ለማስለቀቂያ ገንዘብ የሚጠየቅበት የማልዌር አይነት ነው፡፡ ማልዌር ማለት ማንኛውም ዓይነት ጤናማ የኮምፒውተር ሥርዓትን ለማስተጓጎል እና ለማቋረጥ በጥቃት አድራሾች የሚለማ የሶፍትዌር ዓይነት ነው፡፡
ራንሰም የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አንድን የተያዘ ነገር ለማስለቀቅ የሚጠየቅ ገንዘብ ነው፡፡ ራንሰምዌር ስሙ እንደሚጠቁመው ጥቃት አድራሾች ለዚህ አገልግሎት ያዘጋጁትን ማልዌር በመጠቀም የሚቆልፏቸውን የግለሰብ ወይም የተቋማት መረጃዎችን ለመልቀቅ ብዙ ገንዘብን ይጠይቃሉ፡፡ የሚጠየቀው ገንዘብ ብዙ ጊዜ ምናባዊ የሚባለውን የገንዘብ ዓይነት (Crypto currency) ነው፡፡
ብዙ የራንሰምዌር ዓይነቶች ያሉ ሲኾን ሁሉም ገንዘብ ማግኘት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ ለዛም ነው ፋይሎችን እና የኮምፒውተር ሥርዓትን በማመሥጠር (Encrypt) በማድረግ የተቆለፈውን ፋይል ወይም የኮምፒውተር ሥርዓት ለመክፈት የሚያስችል የመክፈቻ ቁልፍ (decryption key) ለማግኝት ገንዘብ የሚጠይቁት፡፡
በታሪክ ከተከሰቱ የራንሰምዌር የጥቃት ዓይነቶች ውስጥ ሮቢንሁድ የተሰኘው ጥቃት የተከሰተው እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ 2019 ዓ.ም በአሜሪካ የባልቲሞር እና የግሪንቪል ከተሞች ላይ ነው፡፡ ይህ ጥቃት አገልግሎቶችን እና የደኅንነት ፕሮግራሞችን እንዳይሥሩ፣ የመረጃ መረብ ሥርዓቱ ትስስር እንዲበላሽ፣ ቀሪ መረጃዎች (Backup) እንዲጠፉ እና የኮምፒውተሮችን አውቶማቲክ የጥገና አማራጭ እንዳይሠራ በማድረግ ከባድ ኪሳራን ያደረሰ ነው፡፡
በአሜሪካ ከተሞች ለተከሰተው ጥቃት ከ3 እስከ 13 ቢትኮይን (ምናባዊ ገንዘብ) ተጠይቆ ነበር፡፡ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 1 ቢትኮይን ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ስለዚህ የተጠየቀው ገንዘብ ምን ያህል ከባድ እንደኾነ መረዳት ይቻላል፡፡
ከሰሞኑ ሮይተርስ ያወጣው ዘገባ የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር ከአውሮፓውያኑ 2019 ዓ.ም ጀምሮ በደረሰው ጥቃት የ37 ዓመቱ ኢራናዊ ሲና ጎሊንጃድ እጁ እንዳለበት መግለጹን፣ እስከ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ19 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ ማድረሱን እና ለዚህም እስከ 30 ዓመት እስራት ሊጣልበት እንደሚችል ጠቅሷል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን