
ደብረ ብርሃን: ግንቦት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የሥራ አፈጻጸምን ገምግመዋል። በከተማ አሥተዳደሩ ስምንት ጤና ጣቢያዎች እና ሁለት ሆስፒታሎች መኖራቸውን በሪፖርት ያቀረቡት የመምሪያው ኀላፊ በቀለ ገብሬ በተቋማቱ ጽዱ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥባቸው እየተሠራ ነው ብለዋል።
በእናቶች እና በሕጻናት ጤና ዙሪያ የተለያዩ ተግባራት መፈጸማቸውን የገለጹት ኀላፊው ከተማ አሥተዳደሩ በ110 ሚሊዮን ብር እስከ 3ኛ ፎቅ ድረስ የማስፋፊያ ግንባታ በተለያዩ ጤና ጣቢያዎች እየተገነባ መኾኑን ገልጸዋል። የአካባቢውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት በክልሉ ጤና ቢሮ እየተገነባ እና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የደብረ ብርሃን ጠቅላላ ሆስፒታል ተስፋ ሰጭ ነውም ተብሏል። ወረርሽኝን ለመከላከል ከተማው እየሠራ ቢኾንም ካለው ተጋላጭነት አንጻር ድጋፍ ያሻዋልም ተብሏል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበጎ የሚታዩ በርካታ ሥራዎች እንደመኖራቸው ሁሉ ቢስተካከሉ ያሏቸውን አስተያየቶች ሰጥተዋል።
በምክር ቤቱ የሰው ሀብት አሥተዳደርና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል መሰሌ ሞትባይኖር የቆሻሻ አወጋገድ ላይ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሩት አስፋው የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት መከላከል ላይ ጠንካራ ሥራ መሠራት ካልተቻለ አሳሳቢ ነው ብለዋል።
የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በላይ ዘለቀ በበኩላቸው የተቋማት ማስፋፊያ ሥራ ላይ በጎ ተግባራት ቢኖሩም መድኃኒት የተላመደ ቲቢ ሕክምና ክፍልን መገንባት ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን