ሥጋ ደዌ በሽታ በባክቴሪያ እንጅ በዘርም አይተላለፍም፤ እርግማንም አይደለም።

20

ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ የሺመቤት ካሴ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነዋሪ ናቸው። እኒህ ወይዘሮ በሥጋ ደዌ የተጠቁት በ1967 ዓ.ም እንደ ነበር ለአሚኮ ተናግረዋል። በሽታው በተከሰተባቸው ወቅት የተሰማቸውን ስሜት እንዲህ ያስታውሳሉ። አካላቸው ላይ ያልተለመደ ነገር ይሰማቸዋል፤ ቀስ እያለም እንዳሳከካቸው ትውስታቸውን ገልጸውልናል።

ሕመሙ ከቀን ወደ ቀን ይለቀኛል ብለው ተስፋ ቢያደርጉም የሚያሳክካቸው ነገር መቁሰል ይጀምራል፤ ታዲያ አንዳንድ ሰዎች “የቆዳ መቆጣት ነው” ይሏቸው አንደ ነበርም ተናግረዋል። ሕመሙ በጭራሽ ሥጋ ደዌ ይኾናል ብዬ አልገመትኩም ነበር የሚሉት ባለታሪኳ ስለ በሽታው እንኳ ሰምተው እንደማያውቁ ነው የገለጹት። ሕመሙ ሲጠናባቸው ወደ ህክምና ተቋም እንዳመሩ ነው የሚያስታውሱት።

ተመርምረውም በሽታው “ሥጋ ደዌ” መኾኑን ሐኪሞቹ እንደነገሯቸው ነው የገለጹት። መድኃኒት ወዲያውኑም በነጻ ሰጥተውኛል ይላሉ። መድኃኒት ያልወሰደ ህሙማን በሽታውን ለሌሎች ሰዎች እንሚያስተላልፍ ሐኪሞች እንደመከሯቸውም አስታውሰዋል። አሁን ድረስ እርሳቸው ስለ በሽታው ለሰዎች እንደሚያስተምሩ በመግለጽ።

የእኔ ሕመም ሥጋ ደዌ መኾኑን የአካባቢው ነዎሪዎች ቢያውቁም ሳይፈሩ እና ሳያገሉኝ ቤቴ ድረስ በመምጣት እግዚአብሔር ይማርሽ እያሉ ይጠይቁኛል፤ ምግብም ያመጡልኛል ነው ያሉት። በሰርግ እና ክርስትናው ይጠሩኛል እንጂ ከማኀበራዊ ሕይዎት አላገለሉኝም ብለዋል። በጉልበቴ እና በወዜ ጥሬ እና ግሬ ሃብት አፈራሁ የሚሉት ወይዘሮ የሺመቤት በሂደትም የእህል ወፍጮ ቤት መክፈታቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው የእኔን ታክሞ መዳን የተመለከቱ ግለሰቦች መሰል ህመም አለባቸው ብለው የጠረጠሯቸውን ሰዎች እንደ የሺመቤት ታክማችሁ ትድኑ ዘንድ ሐኪም ቤት ሂዱ እያሉ ይመክሯቸዋል ነው ያሉት። ይህም የኀብረተሰቡን ንቃተ ኅሊና ያመላከተ ነው ሲሉም አድንቀዋል። በእርሳቸው ምሳሌነትም የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ታክመው መዳናቸውን በመጠቆም።

እኔ በምኖርበት አካባቢ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችን የሚያገል ሰው የለም ያሉት ወይዘሮ የሺመቤት በሽተኛው ራሱ ሰው ያገለኛል ብሎ ይሰጋል እንጂ ሌላው እንዳሰቡት አይደለም ነው ያሉት። ከመቶ ሰው አንድ ግንዛቤ የሌለው ሰው ቢያገል እንኳ ራሱ የሥጋ ደዌ ህመምተኛው እውነታውን ነግሮ ግንዛቤውን በማሳደግ የተዛባውን አመለካከት ማረም ይገባል ብለዋል።

የሥጋ ደዌ ተጠቂ ብኾንም ላለፉት 20 ዓመታት የእህል ወፍጮ ቤት ከፍቼ ማኅበረሰቡን እያገለገልሁ እገኛለሁ፤ ማኅበረሰቡም የሥጋ ደዌ ተጠቂ በኾነችው የሺመቤት የእህል ወፍጮ ቤት አልገለገልም ብሎ አያውቅም ነው ያሉት ፡፡ ልጆቼን ለቁም ነገር አብቅቻለሁ የሚሉት ወይዘሮ የሺመቤት በዕድር እና ሰንበቴው፣ በዕቁብ እና በጸበል ጻዲቅ ማኅበር በንቃት እየተሳተፉም ይገኛሉ፡፡

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የቲቪ እና ሥጋ ደዌ መከላከል እና መቆጣጠር ኬዝ አሥተባባሪ መንበሩ ፍጹም የስጋ ደዌ በሽታ ሌፕራ በተባለ በዐይን በማይታይ ባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣ ነው ብለዋል፡፡ በዋናነት ቆዳን እና ነርቭን በማጥቃት ለአካለ ጉዳት ይዳርጋል ነው ያሉት። አሁን በዓለም ላይ የሥጋ ደዌ በሽታ እየቀነሰ የመጣ ቢኾንም በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ላይ ያለው ስርጭት የዓለምን 95 በመቶ ይሸፍናል። ከእነዚህ ሀገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት ነው ያሉት።

“ሥጋ ደዌ በሽታ በባክቴሪያ እንጅ በእርግማን እና በእርኩስ መንፈስ አይመጣም፤ በዘርም አይተላለፍም” ያሉት አሥተባባሪው የበሽታው ተጠቂዎች በህክምና ተመርምረው ከተረጋገጠ ፈዋሽ የኾነ መድኃኒት በነጻ እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡ ህክምናውም ከክልል እስከ ጤና ኬላ ድረስ ባሉ የጤና ተቋማት በነጻ ይሰጣል ነው ያሉት አሥተባባሪው።

በሽታው በትንፋሽ አማካኝነት ከአፍንጫ እና ከአፍ በሚወጣ ባክቴሪያ ይተላለፋል ነው ያሉት፡፡ በመኾኑም በሽታው በትንፋሽ የሚተላለፍ እንደመኾኑ መጠን ያልታከሙ ታማሚዎች ጋር ንክኪ የሚያደርጉ ሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ ይገባልቸዋል ብለዋል፡፡ በሥጋ ደዌ የተጠቁ ሰዎች በሽታው በተከሰተበት የሰውነት ክፍል ላይ ነጣ ያሉ ወይም የቀሉ የቆዳ ቁስለቶች ይታያሉ፤ የቆዳ ቁስለት የተከሰተበት አካባቢ ይደነዝዛል ብለዋል፡፡

በጠቅላላው በሽታው ካልታከመ የነርቭ እብጠት፣ የእጅ እና እግር መቆልመም፣ የፊት ገጽታ መቀየር (መበላሸት) እና የጡንቻ መክሳትንም ያስከትላል ነው ያሉት፡፡ አሥተባባሪው እንዳሉት በሽታው ፍቱን መድኃኒት አለው፤ በአግባቡ እና በትክክል መውሰድ ከተቻለ በፍጹም የሚድን እንደኾነ ነው የገለጹት።

ዘጋቢ: ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየከተማዋን ሰላም ዘላቂ እና አስተማማኝ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next article“ከጦርነት አዙሪት መውጣት ያልቻልነው መሠረታዊ ችግሮቻችን ላይ ተመካክረን መፍትሄ ማምጣት ባለመቻላችን ነው” ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ