
ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኪንታሮት ሕመም በርካታ ወገኖችን ያጠቃል። ብዙዎችን በሕመም ውስጥ ያኖራል። በርካታ ወገኖች የኪንታሮት ሕመም ተጠቂ ኾነው ለዓመታት ደብቀው ኖረዋል። ሕመማቸውን ሳይናገሩ በስቃይ ተቀምጠዋል። “ሕመሙን የደበቀ መድኃኒት አያገኝም” እንዲሉ አበው ሕመማቸውን የደበቁ ወገኖች በቂ ሕክምና ሳያገኙ በሕመም ስቃይ ዓመታትን ተሻግረዋል። አንዳንዶችም ኪንታሮት በሕክምና አይድንም ሲሉ ይደመጣሉ።
ለመኾኑ የኪንታሮት በሽታ ይድናል ? ወይስ ? በባሕር ዳር ከተማ አዲስ ዓለም ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ታደሰ ፈንታ የኪንታሮት በሽታን በተመለከተ ማኅበረሰቡ ብዙ ነገሮችን ማወቅ አለበት ይላሉ። ኪንታሮት በታችኛው ፊንጢጣ ክፍል ውስጥ የሚገኙ የደም ሥሮች መወጣጠር፣ የደም ስሮች መቆጣት ወይም እብጠት ምክንያት የሚመጣ ሕመም ነው።
የደም ሥሮች ውጥረት ሲደርስባቸው ያብጣሉ፣ እነርሱ ሲያብጡ የሚከሰት ሕመም ነው ብለዋል። ነገር ግን ይላሉ ስፔሻሊስቱ ከታችኛው ፊንጢጣ የሚነሳ እብጠት ሁሉ ኪንታሮት ነው ማለት አይደለም ብለዋል። ለኪንታሮት ሕመም መነሻ ብዙ ምክንያች አሉ፣ በሆድ ድርቀት የሚጠቁ ሰዎች በኪንታሮት የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው። ማንኛውም የሆድ ድርቀት የሚያመጣ ሕመም ለኪንታሮት መንስኤ ነው። ሽንት በሚሽናበት ወይም ሰገራ በሚወጣበት ከፍተኛ የኾነ ማማጥ ለኪንታሮት መነሳት ምክንያት ይኾናል።
በእርግዝና ወቅትም በፊንጢጣ በኩል መጫጫን ስለሚኖር የደም ስሮች እንዲያብጡ ወይም እንዲቆጡ ያደርጋል። ይህም ለኪንታሮት መነሻ ሊኾን ይችላል። እርግዝና ወይም ወሊድ ለኪንታሮት መፈጠር እንደ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል ነው የሚሉት። ከመጠን በላይ የኾነ ውፍረት እና ክብደታቸው የጨመረ ሰዎች ለኪንታሮት ሕመም ተጋላጭ ናቸው። ከዕድሜ ጋር ተያይዞም የኪንታሮት ሕመም ሊመጣ ይችላል ይላሉ።
ፊንጢጣ አካባቢ ለሌሎች ሕክምናዎች ቀዶ ሕክምና ሲደረግ የደም ዝውውሩን ስለሚነካው ለኪንታሮት ሕመም መነሻ ሊኾን ይችላል። በዘር ምክንያትም ሊከሰት እንደሚችል ነው የተናገሩት። ሦስት አይነት የኪንታሮት አይነቶች እንዳሉ የሚናገሩት ስፔሻሊስቱ አንደኛው ከፊንጢጣ ውስጥ የሚከሰት ኪንታሮት ነው፣ ሁለተኛው ከፊንጢጣ በውጭ በኩል የሚነሳ ኪንታሮት ነው፣ ሦስተኛው ኪንታሮት ደግሞ ውጫዊ እና ውስጣዊ ላይ የሚፈጠር ነው። አንዳንድ ሰው ሁለቱም ሊከሰትበት ይችላልና ነው ያሉት።
ፊንጢጣ ውስጥ የሚከሰት ኪንታሮት አራት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው ደረጃ ፊንጢጣ ላይ የሚፈጠር ደም መፍሰስ ነው፣ ደረጃ ሁለት ሲኾን ሰዎች ሰገራ ሲወጡ እብጠቷ ትወጣለች፣ በራሷም ትመለሳለች። ሦስተኛው ደረጃ እብጠቱ ወደ ውጭ ይወጣል ይህንም በእጅ ወደ ውስጥ መመለስ ያስፈልጋል። በራሱ አይመለስም። አራተኛ ደረጃ ላይ ከኾነ ግን እብጠቱ ወደ ውጭ ሲወጣ ሰዎች በእጃቸውም ለመመለስ አይችሉም።
የኪንታሮት ሕመም ሲኖር የሚታዩ ምልክቶች የመጀመሪያው ደም መፍሰስ፣ ደሙ ከሰገራ ጋር ተቀላቅሎም ሊኾን ይችላል፣ ዝም ብሎም ሊፈስ ይችላል፣ እብጠት ይኖራል። የሕመም ስሜት አለው። በተለይም ውጫዊ ኪንታሮት በጣም ሕመም አለው። የውስጠኛው ብዙ ጊዜ ደም ይፈስሰዋል፣ ግን ሕመሙ ያን ያክል ነው ይላሉ።
የማሳከክ ጸባይ እና ነጭ ፈሳሽም ይኖራል። ሰገራ ወጥተው ሲጨርሱ እንደገና ያልጨረሱ የመምሰል ስሜትም አለው። የኪንታሮት በሽታን ቀድሞ መከላከል ይቻላልን ? ስፔሻሊስቱ እንደሚሉት ኪንታሮትን ቀድሞ መከላከል እና ተጋላጭነትን መቀነስ ይቻላል ይላሉ። ሆድ ድርቀትን መከላከል፣ ይህን ለማድረግ ከስምንት እስከ አሥር ብርጭቆ ውኃ በቀን መጠጣት፣ ፍራፍሬን መጠቀም፣ የአመጋገብ ስልትን ማስተካከል፣ ክብደትን መቀነስ፣ የጎንዮሽ ሕመሞችን መታከም ይገባል ነው ያሉት። በተለይም አመጋገብ እና ክብደትን ማስተካከል ከተቻለ ተጋላጭነትን መቀነስ ይቻላል ብለዋል።
ሰገራ እየደረቀ የሚያስቸግራቸው ሰዎች መድኃኒት እየወሰዱ መከላከል እንደሚቻል ነው የተናገሩት። ማኅበረሰቡ ስለ ኪንታሮት ትኩረት ማድረግ አለበት የሚሉት ስፔሻሊስቱ አንዳንድ ጊዜ የሚመጡ ሕሙማንን ሳይ አለቅሳለሁ ነው የሚሉት። ኪንታሮት በሕክምና ይድናል፣ ማኅበረሰቡ ኪንታሮት በሕክምና አይድንም ብሎ ነው የሚያስበው፣ ነገር ግን ከመለስተኛ ሕክምና እስከ ቀዶ ሕክምና ድረስ ስላለው ይድናል ነው ያሉት።
ነገር ግን ብዙዎች ኪንታሮት ሲያማቸው ወደ ዘመናዊ ሕክምና ከመሄድ ይልቅ ወደ ባሕል ሕክምና መሄድ ይቀናቸዋል። በባሕል ሕክምና የሚሰጡ ሕክምናዎች ለከፋ ችግር ሊያጋልጥ ይችላል። በዚህ ምክንያት ሰገራ እና አየርን መቆጣጠር እስኪያቅታቸው ድረስ ሊታመሙ ይችላሉ። የኪንታሮት ሕመም ሲታይ መታከም እንጂ መደበቅ እንደማይገባም አሳስበዋል። በተደበቀ ቁጥር ወደ ከፋ ደረጃ ሊሄድ ይችላል ነው ያሉት። መደበቅ ለከፋ ችግር እንደሚያጋልጥም አሳስበዋል።
ሰገራ መውጫ አካባቢ ሕመሞች ሲፈጠሩ ወደ ሕክምና መሄድ ይመከራል። ወደ ባሕል ሕክምና መሄድ ፊስቱላ ሊፈጥር እንደሚችልም አንስተዋል። የሚድን ሕመም መኾኑን በማወቅ መታከም እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ኪንታሮት አዳን ብለው ሰገራ እና አየር መቆጣጠር እንዳይችል የሚያደርጉ የባሕል ሐኪሞች አሉ። ይሄን መጠንቀቅ ይገባል ብለዋል። የባሕል ሐኪሞችም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። የጤና ባለሙያዎች እና ተቋማትም ስለ ኪንታሮት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
ወገኖቻችን ግን የኪንታሮት ሕመም ሲሰማቸው ወደ ሕክምና በመሄድ መታከም አለባቸው። መደበቅ አያስፈልግም። ይህ ሊከሰት የሚችል ሕመም ነው። መዳንም ስለሚቻል ሕመሙን ተናግሮ እና ታክሞ መዳን ይቻላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ: ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን