
ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ኩፍኝ በቫይረስ የሚመጣ በሽታ ነው። በሽታው ለከባድ ሕመም፣ ለአካል ጉዳት ብሎም ለሞት የሚዳርግ ነው። ኩፍኝ ማንኛውንም ሰው የሚያጠቃ ሲኾን በዋነኛነት በጨቅላ ሕጻናት ላይ እንደሚበረታ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። የመተንፈሻ አካልን በማጥቃት ወደ መላው ሰውነት መሰራጨት የሚችል በሽታም ነው።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ክፍል አሥተባባሪ ተሠማ ብሬ እንዳሉት ኩፍኝ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከፍተኛ ራስ ምታት፣ ደረቅ ሳል፣ በአፍንጫ የሚፈስ ፈሳሽ፣ የዓይን መቅላት ምልክቶችን ያሳያል። የቆዳ ሽፍታ ከፊት በመጀመር ወደ ሌሎች የሰውነት አካላት የመሠራጨት ባህርይም አለው።
ኩፍኝ በፍጥነት የሚተላለፍ በሽታ ነው።
ከታመመ ሰው ወደ ጤነኛ ሰው በትንፋሽ፣ በሳል፣ በንጥሻ እና በንክኪ ይተላለፋል። በተለይ ክትባት ያልወሰደ ሰው በሽታው ካለበት ሰው ጋር ከተገናኘ በኩፍኝ የመያዝ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። በኩፍኝ በሽታ የተያዙ ሰዎች በሽታውን ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፉ ቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ ይመከራል። ወደ ትምህርት ቤት፣ ሥራ ቦታ ወይም ወደ ሌሎች ቦታዎች ከመንቀሳቀስ መታቀብ ይገባቸዋል።
በኩፍኝ የተያዘ ሰው ሕክምና ካላገኘ በሽታው ከጀመረ ቀን አንስቶ እስከ ጥቂት ቀናት ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች በተጨማሪ ዓመታትን ቆይቶ የሚያስከትላቸውም ጉዳቶች አሉ። በተወሰኑ ሳምንታት ውስጥ የማጅራት ገትር፣ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች፣ የበሽታ መከላከል አቅም መቀነስ እና ተቅማጥን ያስከትላል። በሂደት ደግሞ ሊታከም የማይችል የጭንቅላት ጉዳትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶችን ሊያመጣ ይችላል።
ክትባት የኩፍኝ ዋነኛው መከላከያ መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል። ሁሉም ሕጻናት ክትባት እንዲወስዱ እና አዋቂዎችም ክትባቱን በልጅነታቸው ካልወሰዱ እንዲከተቡ ይመከራል። የኩፍኝ በሽታ አንዴ ከተከሰተ በኋላ የተለየ ሕክምና የለውም። ይሁን እንጂ የበሽታው ምልክቶች እንዲጠፉ እረፍት ማድረግ እና ለውሥብሥብ ሕመም ከሚዳርጉ ጉዳዮች ራስን ማቀብ የሕክምና ሂደቱ አካል ተደርገው ይወሰዳሉ።
የትኩሳት ማስታገሻ እና የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት በመውሰድ የሕመሙን መጠን መቀነስ ይቻላል። ብዛት ያለው ፈሳሽ መወሰድ፣ ለሳል የማይዳርግ ርጥበታማ አየር በማረፊያ ክፍል ውስጥ እንዲፈጠር በማድረግ ከኩፍኝ በሽታ የማገገሚያ ጊዜውን ማፋጠን እንደሚቻልም መረጃዎች ያሳያሉ።
አሁን ላይ በክልሉ በሽታው መኖሩን የክትባት ክፍል አሥተባባሪው ተሠማ ብሬ ገልጸዋል። በሽታውን ለመከላከል ከመደበኛ ክትባት ባለፈ የማጠናከሪያ ክትባት ሲሰጥ ቆይቷል።
በዚህ ወቅትም ከግንቦት 6/2017 ዓ.ም እሰከ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም የሚቆይ የመከላከያ ክትባት በዘመቻ እየተሠጠ ነው። በክትባቱ ዕድሜያቸው ከዘጠኝ ወር እስከ አምስት ዓመት የኾኑ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ተደራሽ ይደረጋሉ።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን