
ባሕር ዳር: ግንቦት04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደም ካንሰር ከደም ሴሎች (ህዋሳት) ላይ የሚነሳ የካንሰር አይነት ነው፡፡ በሰውነት ውስጥ የተለያዩ አይነት ሥራዎችን የሚያከናውኑ የደም ህዋሳት አይነቶች ይገኛሉ። እነዚህ ህዋሳት በአጥንት መቅኒ ውስጥ ተመርተው ወደ ተለያዩ የአካል ክፍሎች በመሰራጨት እስኪሞቱ ድረስ ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡
የደም ካንሰር (ሉኪሚያ) በሚከሰትበት ጊዜ በመቅኒ ውስጥ የሚመረቱት ጤነኛ እና ጠቃሚ የደም ሴል አይነቶች በበቂ መጠን እንዳይመረቱ የሚያደርግ ችግር ነው። ከዚህ በተጨማሪም የካንሰር ሴሎች ከመቅኒ ወጥተው በደም አማካይነት ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጩ አልያም ሊከማቹ ይችላሉ፡፡
ብዙ አይነት የደም ካንሰር አይነቶች የሚገኙ ሲኾን ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ በዝግታ የሚባዙ (የሚያድጉ) ሲኾኑ “ክሮኒክ ሉኪሚያ” ተብለው ይጠራሉ፡፡ በፍጥነት የሚያድጉት የደም ካንሰር አይነቶች ደግሞ አጣዳፊ ሉኪሚያ ወይም “አኪዩት ሉኪሚያ” ተብለው ይጠራሉ፡፡ የደም ካንሰር (ሉኪሚያ) በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ቢችልም አንዳንድ የደም ካንሰር አይነቶች ግን በዋናነት በዕድሜን ወይም በጾታን ለይተው ሊያጠቁ ይችላሉ፡፡
👉 የደም ካንሰር አምጪ ምክንያቶች:-
የደም ካንሰርን የሚያመጡ ምክንያቶች በውል ባይታወቁም አጋላጭ ምክንያት ተደርገው የሚወሰዱት ግን:- ለተለያዩ ኬሚካሎች እና ጨረሮች መጋለጥ፣ የኬሞቴራፒ መድሃኒት ወይንም የጨረር ሕክምና መውሰድ፣ አልፎ አልፎ ከዘረመል ጋር የተያያዙ ወይንም ከመወለድ ጀምረው አብረው የሚኖሩ በሽታዎች እንዲኹም በቫይረስ ኢንፌክሽን የሚመጡ በሽታዎች፣ ሲጋራ ማጨስ እና የመሳሰሉት ተጋላጭነትን ከሚጨምሩ ኹኔታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
👉 የደም ካንሰር ምልክቶች:-
የደም ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ምልክት ሳያሳይ ሊቆይ ይችላል፡፡ ምልክቶች መታየት በሚጀምሩበት ወቅት ደግሞ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ድካም ድካም ማለት፣ አቅም ማጣት እና ራስ ምታት ሊከሰት ይችላል። ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች መጋለጥ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የክብደት መቀነስ፣ ከብብት ውስጥ እና በአንገት አካባቢ የሚገኙ እጢዎች ማበጥ፣ በእንቅልፍ ወቅት የሚከሰት ላብ፣ በተደጋጋሚ የሚከሰት ነስር፣ አጥንት ወይንም መገጣጠምያ ላይ የሚሰማ ሕመም ይከሰታል።
ይሁን እንጅ ምልክቶቹ ከሌሎች ሕመሞች ጋርም ተያይዘው ሊታዩ ስለሚችሉ በቶሎ ወደ ጤና ተቋም ሄዶ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
👉 የደም ካንሰር እና ሕክምናው:-
የደም ካንሰር በሰውነት ውስጥ መኖሩ ከታወቀ እና የካንሰሩ አይነት ያለበት ደረጃ በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ የተለያዩ የሕክምና አማራጮች ይደረጋሉ። ለተቀሩት የደም ካንሰር አይነቶች በተለይም ለአጣዳፊ የሉኪሚያ አይነቶች ግን እንደ አይነታቸው እና ያሉበት ደረጃ የኬሞቴራፒ ሕክምና፣ የመቅኒ ንቅለ ተከላ እና የኢሙኖቴራፒ ሕክምና ሊሰጥ እንደሚችል የአማራ ክልል ጤና ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከደም ካንሰሩ ወይም ከሕክምናው ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ተጓዳኝ ሕመሞችን ለማከም የሚሰጡ የሕክምና እርዳታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የደም ካንሰር በሕክምና የሚያሳየው ምላሽ እንደ ታካሚው እድሜ፣ አጠቃላይ የጤና ኹኔታ፣ የካንሰሩ አይነት እና ደረጃ፣ ከሕክምናው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጓዳኝ ሕመሞች ጽኑነት እና እንደሚከናወነው የሕክምና አይነት ሊለያይ ይችላል።
በመረጃ ምንጭነት የአማራ ክልል ጤና ቢሮን እና የዓለም ጤና ድርጅት ድረ ገጽን ተጠቅመናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን