
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በምሥራቃዊ ህንድና ባንግላዴሽ ከባድ ዝናብና ነፋስ መስተዋሉ ተዘግቧል፤ ይህንን ተከትሎም የከባድ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ተሰግቷል፡፡ ‘‘አምፋን’’ የተሰኘ ነፋስ አዘል ማዕበል በሰዓታት ውስጥ የመሬት መንሸራተት እንደሚያስከትልም ተጠብቋል፡፡
ሁለቱም ሀገራት በቅድመ ማስጠንቀቂያ መሠረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ሌላ ተጋላጭ ያልሆኑ መጠለያዎች አዛውረዋል፡፡ ከማዕበሉ መድረስ አስቀድሞም በከባድ ዝናብ ተመትተዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት ፈተና በሆነበት ወቅት ይህ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ ስጋት መምጣት የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ ጥሏቸዋል፡፡
ህንድና ባንግላዲሽ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ህንፃዎች በጊዜያዊ መጠለያነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን ከኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ጋር በተያያዘ አካላዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ ሰዎችን ወደ መጠለያ ለማስገባት ከተለመደው በበለጠ ተጨማሪ ቤቶች እንዲፈልጉ አስገድዷቸዋል፡፡
በህንድ ምዕራባዊ ቤንጋል ግዛት አንድ ፖሊስ እንደተናገረውም ሰዎች በጊዜያዊነት ወደተዘጋጁት መጠለያዎች ለመሄድ ፍቃደኛ አለመሆናቸው ተነስቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በኮሮና በሽታ እንያዛለን የሚል ፍራቻ መሆኑ ታውቋል፡፡
አምፋን በአስር ዓመት ውስጥ ከተከሰቱት ከባድ ከሚባሉ ማዕበሎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የአየር ትንበያ ባለሙያዎች የባሕር ዳርቻዎች በሰዓት 180 ኪ.ሜ በሚወነጨፈው ማዕበል እንደሚመቱ ይጠበቃል፤ ማዕበሉ እስከ 5 ሜትር ከፍታ ይዞ እየተምዘገዘገ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
የውቅያኖስ ወለል መሞቅ ለማዕበሉ መቀስቀስ በምክንያትነት ተገልጿል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ
በኪሩቤል ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡