የውኃ ዳር ውኃ ጥም …፡፡

216

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ ላይ ተገኝተን ነበር፡፡ በላስታ ወረዳ የተከዜ ተፋሰስ የወረዳው ትልቁ የመስኖ ተስፋ ነው፤ ቀጭን አቨቫ፣ ሲመኑ፣ ኩልመስክ፣ ብልባላ፣ ማውሬ፣ ሸምሀ እና ገነተ ማሪያም ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ መስኖ ሊያለሙ የሚችሉ ወንዞች ናቸው፡፡

በወረዳው ከ160 ሺህ ሕዝብ በላይ እንደሚኖር ከዚያው ያገኘነው መረጃ ያለክታል፡፡ 6 ሺህ 650 አርሶ አደሮች ደግሞ በዘመናዊ እና ባህላዊ የመስኖ ጠለፋ በአብዛኛው ጤፍና ሽንብራ ሰብሎችን በማልማት ተሰማርተዋል፡፡
የላስታ ወረዳ ግብርና ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግዛቸው ቢትወደድ እንደተናሩት 26 ቀበሌዎችን የያዘው የላስታ ወረዳ 24 ሺህ ሄክታር በሰብል የሚለማ መሬት ሲኖረው 1 ሺህ 50 ሄክታሩ ደግሞ በመስኖ እየለማ ይገኛል፡፡
አሁን በወረዳው በመስኖ ከሚለማው በላይ ሁሉንም የላስታ ወንዞችን መጠቀም ቢቻል እስከ 10 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት እንደሚቻል መጠናቱንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ወረዳው በመስኖ ዘርፍ ከራሱ አልፎ ሌሎችን መመገብ የሚችል አቅም ቢኖረውም በአግባቡ ባለመሠራቱ ግን በወረዳው ከሚኖረው 160 ሺህ ሕዝብ መካከል 42 ሺህ የሚሆነው የምግብ ዋስትና ድጋፍ ጠባቂ ሆኗል፡፡

በቀጣይ የመስኖ ሀብት ልማቱን ለማጠናከር ያልተጠገኑ የመስኖ የውኃ መስመሮች (ካናሎች) ወደሥራ እንዲገቡ ማድረግና በቋሚ አትክልትና ፍራፍሬዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ላይ እንደሚሠራም አቶ ግዛቸው አስታውቀዋል፡፡

በወረዳው ከዚህ በፊት ለመስኖ ሥራ ያልዋሉ ስድስት ትልልቅ ወንዞች ቢኖሩም በበጀት እጥረት ሁለቱ ብቻ ወደሥራ እንዲገቡ መደረጉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በፓምፕ በመግፋት፣ በጠለፋና በካናል የሚለሙ ወንዞችን ሥራ ላይ በማዋል የተስተዋሉ መዘናጋቶችን ማስቀረት ደግሞ የቀጣይ ዕቅዳቸው እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

የላስታ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አቶ ዳንኤል ማርየ የላስታ ወረዳ አቀማመጥ ውኃን ማመንጨት በሚችሉ ወንዞች የተከበበ ቢሆንም ተራራማነቱና ሸለቋማነቱ ደግሞ ለማልማት ፈታኝ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡ ‘‘ወንዞችን ለልማት ለመጠቀም ከፍተኛ ወጪ የሚያስፈልጋቸው ናቸው’’ ያሉት አቶ ዳንኤል ለማልማት ምቹ በሆኑ እንደቀበሌ 04 ያሉ አካባቢዎች ላይም ጤፍ እና ሽንብራ የማልማት ልምድ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት አዳዲስ የውኃ ማውጫ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመስኖ ልማት እንዲዘምን የሚያደርግ ከሆነ ግን ቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ ልማቶች ላይ በስፋት ለመሠማራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

ሌላው የላስታ ወረዳ የሳርዝና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አቶ አዲሱ መብሬ 2005 ዓ.ም ጀምሮ መስኖ ለማልማት ከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት ነበራቸው፡፡ በአመልድ አማካኝነት 2011 ዓ.ም ሥራ በጀመረው ፕሮጀክት ደግሞ ፍላጎታቸው እውን ሆኗል፡፡ በቀበሌያቸው በቃቆ፣ ወምበርኮ እና የብልባላ ወንዞች የሚፈስሱ ቢሆንም አሁንም በመስኖ የሚለማው መሬት ውስን እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ቋሚና ጊዚያዊ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፎች ላይ ባለመሠራታቸውም ግን ለውጡን በትክክል ለመግለጽ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡

የላስታ ወንዞች ዛሬም የተሸከሙትን ፀጋ ለአሸዋ ሲሳይ እንደተው ቀጥለዋል፤ በፀሐይ ተንነው መና የሚቀሩ ወንዞች እንደሆኑ ናቸው፡፡ በትንሽ የመስኖ ሥራ መርካትም ችግር እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ‘‘ነገ እንሠራለን’’ የሚሉ አባይ መልሶችና ‘‘ውኃማ አለ’’ የሚሉ አጉል ቁጭቶች ከድህነት አያሻግሩም፡፡ ዛሬ ወንዞቹን ማልማት ግን የተሻለ ነገ ላይ ያደርሳል፤ ወንዝ እየፈሰሰ፣ መሬት ጦም እያደረ የዕርዳታ ስንዴ ተስፋ ማድረግ እንዲህ ዓለም ዕርዳታ ጠባቂ የሆነችበት ጊዜ ሲመጣ የበይ ተመልካች ያደርጋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበዋግ ኽምራና ላልይበላ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መቋረጡ ነዋሪዎችን ለምሬት ዳርጓል፡፡
Next articleእየተሠሩ ያሉ መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ አሳሰቡ፡፡