የማኅበረሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ የጤና አገልግሎትን ለማሳደግ እንደሚሠራ ጤና ቢሮ ገለጸ።

17

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ለዞን ጤና መምሪያዎች እና ባለድርሻ አካላት በጤና አገልግሎት አሰጣጥ የማኅበራዊ ተጠያቂነት የሦስት ዓመት ስትራቴጂ ሰነድ ትውውቅ ተደርጓል። በክልሉም እንዲተገበር ታውጇል።

መድረኩን የከፈቱት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የዓለም ጤና ድርጅት ስድስት የጤና መሠረታዊ ግቦችን በመተግበር የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል የማኅበረሰቡን ተሳትፎ አስፈላጊነት ገልጸዋል።

በአማራ ክልልም ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ የማኅበረሰቡን ተሳትፎ እና ባለቤትነት ለማሻሻል ሥራዎች መሠራታቸውን እና ውጤት መመዝገቡንም አንስተዋል።

ተግባሮችን በስትራቴጂ ነድፎ እና አደራጅቶ መሥራት፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እና ተጠያቂነትን ማስፈን ለማኅበረሰቡ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍ የጥራት፣ የፍትሐዊነት እና የተደራሽነትን ክፍተቶች ለመሙላት የማኅበረሰቡን ተሳትፎ አስፈላጊነት አንስተዋል።

ግልጸኝነት ያለው አሠራርን የመተግበር አስፈላጊነትን የጠቀሱት አቶ አብዱልከሪም ሁሉም መሪ እና ባለሙያ የማኅበረሰቡን ተሳትፎ በማረጋገጥ በኩል የሚቀረው መኾኑን ተናግረዋል።

መፍትሄውም የጤና ማኅበራዊ ተጠያቂነት ስትራቴጂውን መተግበር እና ዘመኑ የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ መጠቀም መኾኑን ተናግረዋል።

ስትራቴጂው ከጤና ሚኒስቴር እና አጋር አካላት ጋር በመተባበር የሚተገበር ነው። የየደረጃው የጤና መሪ እና ሙያተኛ እንዲኹም ማኅበረሰቡ የጤና ተቋማትን በባለቤትነት እየጠበቀ የሚገለገልበት ተቋም እንዲኾን ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የመልካም አሥተዳደር ሪፎርም አሥተባባሪ ፈንታሁን ብርሃኑ የጤና ማኅበራዊ ተጠያቂነት ስትራቴጂ ዓላማ ከዚህ በፊት የወጡትን የአገልግሎት አሰጣጦች ማሳለጥ መኾኑን ገልጸዋል።

ተጠሪ ተቋማት ስትራቴጂውን በመተግበር በጤና ዘርፍ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ተጠያቂነትን እንዲያሰፍኑ እንደሚፈለግም ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ የሚያገኘውን የጤና አገልግሎት እየመዘነ ደረጃ የሚሰጥበት አሠራር መኾኑን እና ተጠያቂነትንም ለማስፈን እንደኾነ ገልጸዋል።

በጤና ተቋማት የሚሰጠውን አገልግሎት ለመመዘን በየቀበሌው የኅብረተሰብ አደረጃጀት እንደሚኖር ነው አቶ ፈንታሁን የገለጹት።

በጤና ሚኒስቴር የተቋማዊ ለውጥ የማኅበረሰብ ተጠያቂነት አማካሪ አንለይ ደሴ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ማለት አገልግሎት ሰጭ፣ ተቀባይ እና መንግሥት በጤና አገልግሎት የሚኖራቸው መስተጋብር እና ለውጥ ማለት ነው ብለዋል።

ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት መመዘኛ ካርድ ሥራ ላይ መዋሉን የጠቀሱት አቶ አንለይ ፕሮጀክቱ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ኅብረተሰቡ ግብረ መልስ እንዲሰጥ ለማድረግ መኾኑንም አክለዋል።

ማኅበረሰቡ የጤና አገልግሎቱን በስድስት ቁልፍ መለኪያዎች በመመዘን የተሰማውን ያነሳል፤ በዚያ ላይም ትንተና ተሠርቶ ተመልሶ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቬይትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ የሚያደርጉትን ይፋዊ ጉብኝት በመቀጠል ከቬይትናም ፕሬዝዳንት ክቡር ጄነራል ሉዎንግ ኩዎንግ እና ከብሔራዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ክቡር ትራን ታንህ ማን ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሃኖይ እየተገነባ የሚገኘውን ትልቅ የዘመነ ከተማ (የስማርት ሲቲ) ፕሮጀክት ጎብኝተዋል። ይኽም ለኢትዮጵያ የከተማ ልማት ሥራ የሚሆን ተመክሮ የመቅሰም ተግባር አካል ነው።