የኢ-ኮሜርስ የንግድ ሥርዓት ለሀገሪቱ የተሻለ ዕድል ይዞ መምጣቱ ተገለጸ።

50

አዲስ አበባ: መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢ-ኮሜርስ የንግድ ሥርዓት ለሀገሪቱ የተሻለ ዕድል ይዞ እንደመጣ አስታውቋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኤሌክትሮኒክስ ንግድ ላይ ለተሰማሩ የተለያዩ ተቋማት ሥልጠና ሰጥቷል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው የኢ-ኮሜርስ ሥልጠና በተለይ እንደ ሀገር የተያዘውን የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ እና ውጤት በማስመዝገብ ረገድ የተሻለ ዕድልን ይዞ የመጣ እንደኾነ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድኤታው ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ.ር) ተናግረዋል።

በተለይ ለንግዱ ማኅበረሰብ ሥልጠና መሰጠቱ የኢ-ኮሜርስ ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድን ወደ መሬት ለማውረድ እና ተግባሩን በማቀላጠፍ ረገድ የጎላ ሚና እንዳለው ተመልክቷል። በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቢዮት ባዩ (ዶ.ር) እንዳሉት ኢ-ኮሜርስ የንግድ ሥርዓት በተለይ እንደ ሀገር ያለውን የዲጂታል የንግድ ሥርዓት ያሳድጋል። ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

ኢ-ኮሜርስ የንግድ ሥርዓት ሀገራዊ የልማት መርሐግብርን ለማሳደግ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና በተለይም የኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል። ዓለም የዲጂታል አብዮት እያካሄደ መኾኑን የጠቀሱት ዶክተር አቢዮት የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ወይም ኢ-ኮሜርስ ለሀገሪቱ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ የቴክኖሎጂ ሥርዓት መኾኑን አመላክተዋል።

በአንድ ሀገር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማትን ማፋጠን የሚቻለው ለዘርፉ አስቻይ የኾነ የሕግ እና የቁጥጥር ማዕቀፍ ሲኖር ነው ያሉት ዶክተር አብዮት እንደ ሀገር የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድሎችን በመጠቀም የሥራ ዕድል መፍጠር እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ ሁሉ አቀፍ እና ቀጣይነት ያለው ሁለንተናዊ ልማትን ማሳለጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የትግራይ ክልል አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት:-
Next article“ሕግን መነሻና መዳረሻ አድርገን ማንነታችንን ለማጽናት እየሠራን ነው” አቶ አሸተ ደምለው