የኢትዮጵያ አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ማጠቃለያ መድረክ እየተካሄደ ነው።

27

አዲስ አበባ: መጋቢት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ማጠቃለያ መድረክ “ከሸማችነት ወደ አምራችነት’ በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ነዉ። በፕሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የፌዴራል እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር አምራቹን ማበረታታት ብቻም ሳይኾን የፋይናንስ አቅርቦትም በማመቻቸት የመሥሪያ እና የማምረቻ ቦታዎችን ማቅረብ፣ የመሠረት ልማትን ማስፋፋት እና አስፈላጊ የሙያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ሥራ ፈጣሪዎችን እየደገፈ ይገኛል ያሉት የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ናቸው፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በርካታ የመሥሪያ እና ማስፋፊያ ቦታዎችን አቅርቧል ነው ያሉት፡፡ የፋይናንስ እና የመሳሪያ ሊዝ አቅርቦትም አመቻችቷል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም በተለያዩ ምክንያቶች ምርት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን በመለየት እና ተግዳሮቶቻቸውን በመቅረፍ ወደ ምርት አቅርቦት እንዲገቡ አድርጓል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በሀገሪቱ ኢኮኖሚ አምራች ኢንዱስትሪዎች መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጡ ለማስቻል መንግሥት ልዮ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል። ገቢ ምርትን በመተካት እና ኤክስፖርትን በማሳደግ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንድኹም የቴክኖሎጅ ሽግግር እንዲመጣ በማስቻል በኩል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በቀጣይም ቅንጅታዊ አሠራርን አጠናክሮ በመቀጠል እና አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ለበለጠ ስኬት በጋራ እንሠራለን ብለዋል ሚኒስትሩ። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኀላፊ ጃንጥራር አባይ መንግሥት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ለዘርፉ ልዮ ትኩረት በመስጠቱ ማነቆ የነበሩ የመሥሪያ ቦታ፣ መሠረተ ልማትን ማሟላት እና የገበያ ትስስር ችግሮችን መፍታት ተችሏል ብለዋል።

ከንቅናቄው በፊት የነበረው የማምረት አቅም 48 በመቶ እንደነበር ገልጸው በንቅናቄው አማካኝነት አኹን ላይ የማመረት አቅም 64 በመቶ መድረሱን አመላክተዋል። ከ250 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ለጎብኝዎች አቅርበዋል።

ዘጋቢ: ኢብራሂም ሙሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“በሀገር ደረጃ ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ለውጥ መጥቷል” ግርማ አመንቴ (ዶ.ር)
Next articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት፦