ሳምንቱ በታሪክ

33

✍የአንድነት ገመድ

ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ 13 ዓመታት ተቆጥረዋል።

ግንባታው በዚህ ሳምንት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ሲጀመር ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም የሚገነቡት እና በአምስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር። ኾኖም ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች ተጓትቷል።

ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ግን የግንባታውን ችግሮች በመፍታት፣ ግንባታውን ቀጥሏል።

ግድቡ በአሁኑ ወቅት 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የያዘ ሲኾን፣ ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ይይዛል ተብሎም ይጠበቃል። ፕሮጀክቱ በ2017 ዓ.ም ተጠናቆ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሎም ይጠበቃል።

ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ከፍተኛ የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል። ባለፉት 13 ዓመታት ከ19 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይም ተሠብሥቧል።

✍ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ እረፍት።

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ሚያዝያ 22 ቀን 1868 ዓ.ም በእነዋሪ ከተማ ተወለዱ። የአባታቸው ዳግማዊ ምኒልክን ዙፋንን በመውረስ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም በ41 ዓመታቸው የኢትዮጵያ ንግሥተ ነገሥታት ኾነዋል።

የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም በአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዐ መንግሥት ተቀብለው ዘውድም ጭነዋል።

ከ1909 እስከ 1922 ዓ.ም በዘለቀው የንግሥና ዘመናቸው ከአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ጋር በመኾን ኢትዮጵያን በጋራ አሥተዳድረዋል።

በዚህ ወቅት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ለሴቶች በተለይም በወሊድ ወቅት የሚደርስባቸውን ችግር በመገንዘብ የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልን በማቋቋም የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ጥረት አድርገዋል።

በተጨማሪም በዘመነ መንግሥታቸው ባርነትን ለማስወገድ ከፍተኛ ዘመቻ በማካሄድ የተወሰኑ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትንም ተሳትፎ በማሳደግ በንግሥናቸው ዘመን የዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) አባል ኾናለች።

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም በታላቁ ቤተመንግሥት ያረፉ ሲኾን አጽማቸውም ከአባታቸው ጋር በታኣካ ባዕታ ለማርያም ገዳም በክብር አርፏል።

✍ዘመናዊ የኦሎምፒክ አጀማመር!

እ.ኤ.አ ኤፕሪል 6፣ 1896 የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በግሪክ አቴንስ ተጀምረዋል። የኦሎምፒክ ጨዋታዎች መነሻ በጥንቷ ግሪክ ሲኾን ከ776 ዓ.ዓ እስከ 393 ዓ.ም ድረስ በየአራት ዓመቱ ይካሄዱ ነበር።

ዘመናዊውን ኦሎምፒክ የማስጀመር ሐሳብን ያመነጨው ፈረንሳዊው ፒየር ደ ኩበርቲን ነበር። ደ ኩበርቲን ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድርን በማዘጋጀት በሀገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና ሰላምን ለማስፈን ፈልጎ ነበር ያስጀመረው።

ጨዋታዎቹ የተካሄዱት በአቴንስ በሚገኘው ፓናቲናይኮስ ስታዲየም ነበር።

በጨዋታዎቹ ላይ 14 ሀገራት የተሳተፉ ሲሆን፣ ከ200 በላይ አትሌቶች ተወዳድረዋል። በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ አይነት ስፖርቶች ተካተዋል እነዚህም አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ፌንሲንግ፣ ጂምናስቲክስ፣ የተኩስ ውድድር፣ ዋና፣ ቴኒስ፣ ክብደት ማንሳት እና ትግል ነበሩ።

ግሪክ በጨዋታዎቹ ብዙ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። አሜሪካ እና ጀርመን በሁለተኛ እና በሦስተኛ ደረጃ ጨርሰዋል።

የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ዓለም አቀፍ አንድነትን፣ ሰላምን እና የስፖርት መንፈስን የሚያንፀባርቁ ናቸው።

የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች በዓለም የስፖርት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ክስተቶች ናቸው። የአለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (IOC) ድረ-ገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፌደራል መሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የእግር ኳስ ጨዋታ አካሄዱ።
Next article“ስለ ሀገር ይመክራሉ፣ ስለ ሕዝብ ይዘክራሉ”