
ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጡት ካንሰር በሰውነት ክፍሎች ውስጥ መሞት የሚገባቸው ሴሎች ሳይሞቱ ጊዜውን አልፈው ከቁጥጥር ውጭ በመራባት ጡትን እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን ሲወርሩ የሚከሰት በሽታ ነው፡፡ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የኾናቸው ሴቶች ላይ እንደሚበረታ እና እድሜ ሲጨምርም በበሽታው የመጠቃት መጠኑ እንደሚጨምር ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ወይዘሮ ግርማነሽ ተገኘ በባሕር ዳር ከተማ በላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በባለሙያዎች አማካይነት ስለ ጡት ካንሰር ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ በማድረግም ነጻ መኾናቸውን አረጋግጠዋል። የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ቤት ለቤት ያስተምራሉ፤ ለበሽታው ከሚያጋልጡት በመጠንቀቅ ምልክቶቹ ሲታዩም ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሕክምና ማግኘት እየተለመደ መኾኑን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ ስለ ጡት ካንሰር አደገኛነት ግንዛቤ እንዲኖረው በሴቶች ልማት ኅብረት አደረጃጀት ትምህርት እየተሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል። ተመርምረው ከጡት ካንሰር ነጻ መኾናቸውን ያረጋገጡት ወይዘሮ ግርማነሽ ሴቶች በየጊዜው ለጤናቸው ትኩረት ሰጥተው መመርመር በተለይም የነጻ ምርመራ እና ሕክምናውን በአግባቡ በመጠቀም ሕይዎታቸውን ሊታደጉ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የሕክምና እና ተሃድሶ አገልግሎት ቡድን አሥተባባሪ መሠረት ባንቲገኝ የጡት ካንሰር ምርመራ እንደሚሰጡ ገልጸዋል። ስለ ጡት ካንሰር ትምህርት እየተሰጠ ቢኾንም ሴቶች በብዛት እየተመረመሩ አለመኾኑንም ነው የገለጹት። የቤተሰብ ጤና ቡድኖች ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ በሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት ተላላፊ ባልኾኑ በሽታዎች ቡድን የካንሰር እና ማኅጸን በር ካንሰር ተጠሪ ዶክተር ቴዎድሮስ ጌታቸው ለአሚኮ በሰጡት ማብራሪያ የጡት ካንሰር በሽታ ምልክቶች የሚታዩት በሽታው ከተከሰተ በኋላ ቆይቶ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ጡት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሲታይ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡
በጡት ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ ዕጢዎች እና እብጠቶች መኖራቸውን የገለጹት ዶክተር ቴዎድሮስ ካንሰር እብጠቱ እና ደረጃው ከፍ ሲል የሚታዩ ምልክቶች የጡት ቅርጽ ለውጥ፣ የቆዳ መሸብሸብ ወይም መወፈር፣ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መግባት፣ ደም መሰል ፈሳሽ መኾናቸውን ጠቅሰዋል። የጡት ካንሰር በዓይን ከሚታዩ ምልክቶች፣ ሴቷ በግሏ ከምታደርገው ክትትል፣ በጤና ተቋም ከሚደረግ ምርመራ በተጨማሪ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ከፍተኛ ምርመራዎች መኖራቸውን ዶክተሩ ገልጸዋል።
በሽታው ብዙ ጉዳቶች እንዳሉት የጠቀሱት ዶክተር ቴዎድሮስ ሕመም ሲጀምር እና ሲቆስል ያለው ስቃይ፣ ለሕክምና መመላለስ፣ የጡት መቆረጥ እና ማኅበረሰባዊ መገለል ሲብስም ሞት እንደሚያስከትል ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ከካንሰር ዓይነቶች ከፍተኛውን ደረጃ (32 በመቶ) የሚይዘው የጡት ካንሰር መኾኑን በሆስፒታሎች ደረጃ እና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ያመላክታሉ።
በ2002 ዓ.ም ግሎቮካን በተባለ ድርጅት በተደረገ ጥናት በየዓመቱ 16 ሺህ ለጡት ካንሰር የቀረቡ ምልክቶች መገኘታቸውን እና በጡት ካንሰር በየዓመቱ 9ሺህ የሚኾኑ ሰዎች እንደሚሞቱ ገልጸዋል። የስርጭት መጠኑም ከፍተኛ መኾኑን ያሳያል ብለዋል። ሌላው የበሽታው አስቸጋሪነት ኅብረተሰቡ የሕመም ምልክት ካላየ በስተቀር ወደ ጤና ተቋም ሂዶ የመመርመር ልማዱ ዝቅተኛ መኾኑ ነው።
በሀገራችን 70 በመቶ በላይ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ወደ ጤና ተቋም የሚሄዱት የበሽታው ደረጃ ሦስት እና ከዚያ በላይ ሲኾን ነው። ይህም በቀላል ቀዶ ጥገና ማዳን የማይቻልበት ይኾናል ነው ያሉት፡፡ በሽታው ካለው አደገኛ ባህሪ አንጻር ትኩረት ሳያገኝ መቆየቱን የገለጹት ዶክተር ቴዎድሮስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕክምናው በጤና ጣቢያ ደረጃ መጀመሩን ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮም የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል። ከሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር የቅድመ ምርመራ ሥራ እየተሠራ መኾኑን እና በመጀመሪያው ዙርም 3ሺህ ሰዎች ተመርምረው 16 ኬዝ መገኘቱን ነው ዶክተር ቴዎድሮስ የገለጹት።
የመከላከል ሥራውን በደረጃ 1 እና 2 ላይ እያለ ሕክምናውን ለማስጀመር እየሠራን ነው ብለዋል። ከ30 ዓመት በላይ የኾናቸው ሴቶች ምንም ዓይነት ምልክት ባያዩም በጤና ተቋም ምርመራ ማድረግ እንደሚጠቅማቸው መክረዋል። የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም በመተጋገዝ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሲጋራ እና አልኮልን መጠቀም፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ጤናማ ያልኾነ አመጋገብ ለካንሰር አጋላጭ መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አብዛኛዎቹ በሽታዎች ሲጀምሩ የሕመም ስሜት ስላላቸው ታማሚው ወደ ጤና ተቋም ይሄዳል፤ የጡት ካንሰር ግን ምልክቱ የሚታየው በሽታው እየከፋ እና ጉዳቱ እየጎላ ሲመጣ በመኾኑ አደጋው የከፋ ነው ብለዋል ዶክተር ቴዎድሮስ፡፡
ማኅበረሰቡ በተለይም ሴቶች በአቅራቢያቸው ባለ የጤና ተቋም በመመርመር ጤናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
ዘጋቢ: ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!