
ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የተከሰቱት ግጭቶች ከመፈናቀል እና ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ችግር አስከትሏል። በሁከት፣ በቤተሰብ አባላት መጥፋት፣ ንብረት በመውደም እና ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀል ምክንያት በርካታ ግለሰቦች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ለአሚኮ ሀሳባቸውን ያጋሩት ግለሰብ ትንሽ ወንድማቸው በአካውንቲንግ ተመርቆ ወደ ቤተሰብ ከተቀላቀለ ብዙ አልቆየም፡፡ ሥራ በማፈላለግ ጊዜየን አላጠፋም በማለት በቤተሰብ ድጋፍ ከብት ማድለብ ጀመሮ ነበር ይላሉ ባለታሪኳ፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በአካባቢያችን ለአራት ቀናት ያክል የቆየ ጦርነት ተካሄደ የሚሉት ግለሰቧ በነዛ ቀናት ውስጥ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳናደርግ ቤት ውስጥ ነው ያሳለፍነው፤ አኹን ካሁን ችገሩ በእኛ ቤት ላይ ሊኾን ይችላል በሚል ጭንቀት እንደቆዩም ይናገራሉ፡፡
በአራተኛው ቀን የተኩስ ድምጽ መሰማት ያቆመ ቢኾንም ወንድማቸው ከቆይታ በኋላ የወጣው ወንድማቸው ለህልፈት መዳረጉን እና ቤተሰቡም ከባድ ሀዘን ውስጥ መውደቁን ነግረውናል። የገጠመውን ሀዘን ተከትሎ ሌላኛው ወንድማቸው የወንድሙ ድንገተኛ ሞት እና ከእናቱ የየቀን ለቅሶ ጋር ተዳምሮ ውስጡን ያስጨንቀው እንደነበር እና ዝምታን ያበዛ እንደነበር ነግረውናል፡፡
በተለይ ከወንድሙ ሞት በኋላ ምንም አይናገርም አልፎ አልፎ ጦርነቱ መቸ ነው የሚያበቃው እያለ ይናገር እንደነበርም ገልጸዋል። ከአንድ ሳምንት በፊት ወንድሜን ለምንድን ነው የገደሉት? ምን አደረጋቸው? እናቴ ሁልጊዜ ታለቅሳለች እሷን ሳይ በጣም ይጨንቀኛል ብሎኝ ነበር የሚሉት ባለታሪካችን ከቀናቶች በኋላ ከቤት ጠፋን፤ በስንት ፍለጋ አብዶ እጅ እና እግሩ ታስሮ እየጮኸ አገኘነው ብለዋል።
አኹን ወደ ዐዕምሮ ሕክምና ለመውሰድ እራሴን እያዘጋጀሁ ነውም ብለዋል። የዐዕምሮ ጤና ችግሮች በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ከእነዚህ መካከል ተፈጥሮአዊ፣ ሥነልቦናዊ እና ማኅበራዊ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የዘር ተፅዕኖ፣ የዐዕምሮ ህዋስ መዋቅር ችግር፣ የአንጎል ውስጥ ቅመሞች መዛባት፣ ስር የሰደዱ አካላዊ በሽታዎች፣ አደጋዎች፣ ሱስ እንዲኹም በእናት ማህፀን ውስጥ እና በወሊድ ወቅት በሕጻኑ ላይ የሚደርስ ጉዳት የዐዕምሮ ችግሮችን ሊያስከትሉ ከሚችሉ ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች መካከል የሚጠቀሱት ናቸው ይላሉ በአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዐዕምሮ ጤና ሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ድጋፍ ባለሙያ ቃልኪዳን ኃይሌ።
በሥነልቦናዊ ምክንያቶች ደግሞ ተደጋጋሚ የዐዕምሮ ውጥረቶች፣ በልጅነት የሚገጥሙ ግፍ እና መከራ፣ ፆታዊ እና አካላዊ ጥቃቶች እና ወላጅን በልጅነት በሞት ማጣት በአጋላጭነት ተመዝግበዋል። በተመሳሳይ ጦርነት፣ ስደት፣ አሉታዊ ማኅበራዊ መስተጋብር፣ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ ከሥራ መሰናበት፣ ፍች እና የትዳር አጋርን በሞት ማጣትም የዐዕምሮ ጤና ችግርን ሊያስከትሉ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው።
የዐዕምሮ ሕመም ማንኛውንም የማኅበረሰብ ክፍል እና በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል።በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ከፍተኛ የዐዕምሮ ጤና አስከትሏልም ይላሉ። ግለሰቦች በተለይም በግጭቱ በቀጥታ የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጭንቀት እና ድብርት ላይ መኾናቸውን ሪፓርቶች ያሳያሉ።
እንደ ሕጻናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን ያሉ ተጋላጭ ቡድኖች በተለይ ተጎጂዎች ሲኾኑ ለስሜት እና ለባህሪ መታወክ ይጋለጣሉ ይላሉ። በአሰቃቂ ኹኔታ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ለተለያዩ አይነት የዐዕምሮ ሕመሞች ተጋልጠዋል። በአጠቃላይ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ60 ሺህ በላይ የዐዕምሮ ሕመሞች ከጤና ተቋማት ሪፓርት መደረጋቸውን ባለሙያው ገልጸውልናል።
በ2016 ዓ.ም ብቻ በአማራ ክልል ከሚገኙ የጤና ተቋማት ከ10 ሺህ በላይ ራስን የማጥፋት ሙከራ እና 488 ራሳቸውን አጥፍተው የተገኙ መመዝገባቸውን ነው የጠቆሙት። ይህ ቁጥር የሚያሳየው ወደ ጤና ተቋም የደረሱ እና መርዝን የተጠቀሙ ብቻ ሲኾኑ በሌላ ዘዴ የተጠቀሙ እና ወደ ጤና ተቋም ያልደረሱትን አይጨምርም ብለዋል።
እነዚህ አስደንጋጭ አሐዞች እያደገ የመጣውን የዐዕምሮ ጤና ቀውስ አፋጣኝ ርምጃ የሚያስፈልገው መኾኑን ያሳዩናል ይላሉ ባለሙያው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የጤና ተቋማት፣ የመንግሥት አካላት፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የሚዲያ አካላት፣ የትምህርት ተቋማት እና የዐዕምሮ ጤና ባለሙያዎችን ያካተተ የትብብር አካሄድን ይጠይቃል።
የዐዕምሮ ጤና አገልግሎቶችን ማጠናከር፣ ራስን ማጥፋትን መከላከል ፕሮግራሞችን ከመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ ጋር ማቀናጀት እና የጤና ባለሙያዎችን ተገቢውን ሕክምና መስጠት እንዲችሉ ማሠልጠን አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ማኅበረሰቡን መሠረት ያደረጉ የድጋፍ ፕሮግራሞችን ማስፋፋት፣ ለተሻለ የፖሊሲ ምላሾች የመረጃ አሠባሠብን ማሻሻል፣ እና የሃይማኖት መሪዎችን በዐዕምሮ ጤና ጉዳይ ላይ ማሳተፍ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ይህንን ጉዳይ በብቃት ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ስትራቴጂ ያስፈልጋል። የዐዕምሮ ጤና መስጫ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት፣ ማኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እና የሥነ ልቦና ማኅበራዊ ድጋፍ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ የራስን ሕይወት ማጥፋትን ለመቀነስ ይረዳል። ይህንን አደገኛ አዝማሚያ ለመቀልበስ የሁሉም ባለድርሻ አካላት አፋጣኝ ርምጃ እና ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!