
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኦፕን ኤ.አይ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2015 ዓ.ም በዓለማችን ትልቅ ሥም ባላቸው ሥራ ፈጣሪዎች እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ላይ ምርምር በሚያደርጉ ግለሰቦች የተመሠረተ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ከምስረታው ጀምሮ አምስት ጊዜ ማሻሻያ የተደረገበትን ቻት ጂፒቲ የተሰኘ ቻት ቦት ለዓለም በማበርከት ለተለያዩ ተግባራት ማሳለጫ ኾኖ እያገለገለ ያለን የሰው ሠራሽ አስተውሎት አበርክቷል፡፡
ቻት ጂፒቲ በጽሑፍ በሚደረግ ተግባቦት ከኮምቲውተሮቻችን ጋር በማውራት የተለያዩ ሥራዎችን እንድናከናውን ይረዳናል፡፡ በዋናነት የይዘት ሀሳቦችን በማመንጨት፣ ሒሳብን በማስላት እና የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን በመቀመር የሰዎችን ሕይወት የሚያቀል እገዛን ያደርጋል፡፡ ቻት ጂፒቲ እስከ አኹን በተደረገለት የዝማኔ ማሻሻያ ጂፒቲ 3፣ ጂፒቲ 3 ነጥብ 5፣ ጂፒቲ 4 እና ጂፒቲ ቱርቦ የሚባሉ ሂደቶችን አልፏል፡፡
ከቀናት በፊት ይፋ የተደረገው ደግሞ ጂፒቲ 4 ነጥብ 5 ይሰኛል፡፡ አኹን የደረሰበት ለውጥ እጅግ የላቀ የሚባል ማሻሻያዎችንም ያካተተ ነው፡፡ አዲሱ ቻት ጂፒቲ የላቀ የስሜት ብልህነትን (Enhanced Emotional Intelligence) የተላበሰ በመኾኑ ከሰዎች ጋር ተፈጥሯዊ ሊባል በሚችል መንገድ ተግባቦት ማድረግ ይችላል፤ አኹናዊ የድረ ገጽ መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችል ሥርዓት ስላለውም ተለዋዋጭ ኹኔታዎችን መረዳት ይችላል፡፡
የፈጠራ ሀሳብን የማመንጭት አቅሙ ስላደገ ጥሩ የጽሑፍ ይዘቶችን ማዘጋጀት ይችላል፤ በመማር ሂደቱ (Learning Process) ብዙ የቋንቋ እና የባሕል አውድን የሚረዳ በመኾኑ የተሻለ አውድ የመረዳት ብቃት አለው፡፡ በተጨማሪም በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ከእውነታ እና ዐውድ የራቁ የመረጃ ቅንብሮች (Hallucination) እንዳይኖሩ ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ