
ባሕር ዳር: የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ማለት እንደማንኛውም ካንሰር የሰውነት ክፍል ከቁጥጥር ውጭ በኾነ ኹኔታ ከማህፀን በር ጫፍ ላይ ያሉ ሴሎች ወይም ህዋሳት መብዛት ነው። በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ ሂውማን ፓፒሎማ (HPV) በሚባል ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት በሽታ ነው። ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ እና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ሲኾን ካንሰሩ የሚከሰተው በቫይረሱ ከተያዙ ከረጅም ዓመታት በኋላ ነው። በዚህም በተለይ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ ያሉ እናቶች የቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል።
በኢትዮጵያ በዓመት ከ8 ሺህ በላይ ሴቶች በማህፀን በር ካንሰር በሽታ ይያዛሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 6 ሺህ የሚኾኑት በሞት እንደሚለዩ መረጃዎች ያሳያሉ። ለበሽታው መንስዔ ናቸው ተብለው ከተቀመጡት ምክንያቶች ውስጥ በለጋ ዕድሜ የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመር፣ ከብዙ ወንዶች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም፣ በአባላዘር በሽታ መጠቃት፣ የሰውነት በሽታ መከላከል አቅም መዳከም እና ሌሎች ተዛማጅ በሽታዎች ይጠቀሳሉ።
በበሽታው የተያዙ ሴቶች ደግሞ ያልተለመደ የደም መፍሰስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ያልተለመደ መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ መኖር፣ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ደግሞ የእግር ማበጥ፣ የኩላሊት በሽታ እንዲኹም ሽንት እና ሰገራ ላይ ደም መቀላቀል የመሳሰሉ ምልክቶችን ያሳያሉ። በሽታውን አንድ ለአንድ በመወሰን፣ በለጋ ዕድሜ ከግብረ ስጋ ግንኙነት በመታቀብ፣ መደበኛ የማኅጸን ምርመራ እና ክትባት በመከተብ መከላከል ይቻላል።
በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በሽታውን ለመከላከል የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራ እና ክትባት ሲሠጥ መቆየቱን የክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶች እና ሕጻናት ጤና ባለሙያ ዶክተር ፍቃዴ ጌታቸው ገልጸዋል። እንደ ዶክተር ፍቃዴ ገለጻ በበጀት ዓመቱም ከ9 እስከ 14 ዓመት የዕድሜ ክልል ለሚገኙ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ልጃገረዶች ክትባት እንዲሰጥ በተደረገው ዘመቻ ከ90 በመቶ በላይ ለሚኾኑ ልጃገረዶች ክትባት መሰጠቱን ተናግረዋል።
ክትባቱ በክልሉ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች በዘመቻ ተሰጥቷል። ዶክተር ፍቃዴ እንዳሉት የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ከሌሎች ካንሰሮች የሚለየው ቀድሞ በመለየት ማከም መቻሉ እና ክትባት የተዘጋጀለት መኾኑ ነው። ክትባቱ በሌሎች ሀገራት በዕድሚያቸው ከፍ ላሉ ሴቶች እና ወንዶችም ጭምር የሚሰጥ ነው።
ክትባቱን ከእዚህ በፊት የወሰዱት ተማሪ ህሊና ደሳለኝ እና ተማሪ ሰርኬ በለጠ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ መከላከያ ክትባት ጠቀሜታው ከፍተኛ መኾኑ በመረዳት ክትባቱን መውሰዳቸውን ተናግረዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የማህፀን ጫፍ በር ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኝ በሽታ ነው።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!